አዲስ አበባ፣ ሰኔ 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሶማሌ ክልል የሚንቀሳቀሱ የመንግስትና የግል ባንኮች የስራ እድል ፈጠራ እና የኢንቨስትመንት ስራዎችን እንዲደግፉ ተጠየቀ።
የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሞሀመድ በክልሉ አገልግሎት ከሚሰጡ የመንግስትና የግል ባንኮች ጋር ውይይት አካሂደዋል፡፡
በክልሉ የስራ እድል ፈጠራን ለማሳደግ የሚያስችል አዲስ ስትራቴጂ ተነድፎ ወደ ስራ መግባቱ የተገለፀ ሲሆን በክልሉ የሚገኙ ባንኮች ይህን የስራ እድል ፈጠራ እቅድ በመደገፍ የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ተብሏል፡፡
በመድረኩ ላይ በክልሉ የሚገኙ ባንኮች የብድር አቅርቦት ያለበት ሁኔታ በተመለከተ ግምገማ የተደረገ ሲሆን በክልሉ ያሉ ባንኮች ለክልሉ ተወላጆች የሚሰጡትን ብድር እንዲያሳድጉ መልዕክት ተላልፏል።
በውይይቱ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሙስጠፋ ሞሃመድን ጨምሮ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኢብራሂም ኡስማን እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት መሳተፋቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡