አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በዓለም የአዕምሯዊ ንብረት ድርጅት 64ኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ እየተሳተፈች ነው፡፡
ጉባዔው የድርጅቱ ዋና መ/ቤት መቀመጫ በሆነችው ስዊዘርላንድ ጄኔቫ ከሰኔ 29 ጀምሮ እስከ ሐምሌ 7 ቀን 2015 ይካሄዳል፡፡
በጉባኤው የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ወልዱ ይመስል እና በተመድ የጄኔቫ ቢሮ የኢፌዲሪ ቋሚ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ጸጋአብ ክበበው ተሳትፈዋል፡፡
አቶ ወልዱ ይመስል ÷ ዓለም አቀፉ የአዕምሯዊ ንብረት ድርጅት ውጤታማና ዕድገትን መሰረት የሚያደርግ በተለይም ዝቅተኛ የዕድገት ደረጃ እያስመዘገቡ የሚገኙ ሀገራትን የሚደግፍ ሥርዓት ተግባራዊ እንዲሆን ቁልፍ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ሀገር በቀል የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ተጨባጭ ውጤቶች እየተመዘገቡና በአዕምሯዊ ንብረት ዘርፍም የተመቻቸ ሥርዓት ለመፍጠር እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ብሔራዊ የአዕምሯዊ ንብረት ፖሊሲን ለማጽደቅና እንደ “ማድሪድ ፕሮቶኮል” ያሉ ዓለም አቀፍ ሥምምነቶችን በመቀበል ተግባራዊ ለማድረግ የዘርፉን የሕግ ማዕቀፎች የማሻሻል ሥራዎችበትኩረትና በቁርጠኝነት እየተሠሩ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል የማኅበረሰብ ዕውቀት ጥበቃ ኅግን በራስ ዐቅም ለማዘጋጀት ሥራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙም አውስተዋል፡፡
ከዚሁ ጎን ለጎን የጂኦግራፊያዊ ምንጭ አመላካች ምርቶች ጥበቃ ሥርዓት ለመዘርጋትና የሕግ ማዕቀፍ ለማዘጋጀት የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ መደረጉን አስረድተዋል፡፡
የልዑካን ቡድኑ አባላት ከድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዳረን ታንግ ጋር እንደሚገናኝና ሌሎች የጎንዮሽ ውይይቶችን እንደሚያደርግም ከባለሥልጣኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡