አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የታይፎይድ ህመም የሚከሰተው ሳልሞኔላ ታይፊ በተባለ ባክቴሪያ ነው።
እንደ ህክምና ባለሙያዎች ገለፃ ባክቴሪያው በተበከለ ምግብ፣ መጠጥ ወይም ውሃ የሚተላለፍ ሲሆን÷ በሳልሞኔላ ታይፊ የተያዙ ሰዎች ባክቴሪያውን በአንጀታቸውና በደማቸው ውስጥ ይሸከማሉ።
ባክቴሪያው እጅን በአግባቡ በማይታጠብ ሰው የተዘጋጁ ምግቦችን ወይም መጠጦችን ከወሰዱ የታይፎይድ ትኩሳት ሊያዙ ይችላሉ።
የታይፎይድ ህመም የመጀመሪያ ደረጃ ምልክቶችም የሆድ ህመም፣ ትኩሳት እና አጠቃላይ የህመም ስሜት ሊሆኑ እንደሚችሉ ከጥቁር አንበሳ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የታይፎይድ ትኩሳት እየተባባሰ ሲሄድ ብዙውን ጊዜ ምልክቶቹ ከፍተኛ ትኩሳት ፣ ራስ ምታት፣ የሆድ ህመም፣ የሆድ ድርቀት ቀጥሎም ተቅማጥ፣ በሆድዎ ወይም በደረትዎ ላይ ትንሽ ቀይ ነጠብጣቦች፣ የምግብ ፍላጎት ማጣት እና የድካም ስሜት ናቸው፡፡
እንዲሁም ሰገራ ላይ ደም ማየት፣ ብርድ ብርድ ማለት፣ ከባድ ድካም፣ ትኩረት የመስጠት ችግር፣ ግራ መጋባት እና ቅዠትም በታማሚዎች ላይ ይስተዋላል።
መከላከያ መንገዶቹም እጅን በውሃ እና በሳሙና ቶሎ ቶሎ መታጠብ፣ ውሃን አክሞ መጠቀም፣ ያልበሰሉ ምግቦችን አለመመገብ እና ምግብን በትኩሱ መመገብ እንደሆኑ የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡