አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በፖርቹጋል የሚገኙ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ የተለያዩ ዘርፎች ላይ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ።
ባለሐብቶቹ በኢንዱስትሪ ፓርኮችና በድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠና መዋዕለ ነዋያቸውን ማፍሰስ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡
አዳዲስ ኢንቨስትመንት ስበት ላይ ትኩረት ባደረገው ውይይት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ፣ የድሬዳዋ ከተማ ከንቲባ ከድር ጁሃር፣ የሐዋሳ ከተማ ከንቲባ ፀጋዬ ቱኬ እንዲሁም የፖርቹጋል ንግድና እና ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ ሀላፊ አምባሳደር ክርስቲና ፑካሪንሆ ተገኝተዋል፡፡
በመድረኩ በኢትዮጵያ በተለይም በኢንዱስትሪ ፓርኮችና በድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠና ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች፣ ምቹ መሰረተ ልማቶችና የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
ውይይቱ ከኢንቨስትመንት በተጨማሪ በኢንዱስትሪ ፓርኮችና በከተሞች መካከል ስላለው አዎንታዊ መስተጋብር ልምድና ተሞክሮ የሚወሰድበት መድረክ መሆኑን የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡
በኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ የተመራ ልዑክ በአዲስ አበባ የፓርቹጋል አምባሳደር ሉዊዛ ፍራጎሶ ጋር በኢንቨስትመንትና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመስራት ከስምምነት መድረሳቸው ይታወሳል፡፡