የሀገር ውስጥ ዜና

በደቡብ ክልል የፊታችን ሰኞ 110 ሚሊየን ችግኝ ይተከላል

By ዮሐንስ ደርበው

July 12, 2023

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል ከ9 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ ሰዎች የሚሳተፉበት የ110 ሚሊየን ችግኝ ተከላ የፊታችን ሰኞ ይካሄዳል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪ እና የደቡብ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ኡስማን ሱሩር እንደገለጹት፥ የሚተከሉት ችግኞች የደን፣ የጥምር ደን፣ ቀርከሃ፣ ፍራፍሬ፣ ቡና እና ሌሎችም ናቸው።

በአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩም፥ ተማሪዎች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የሐይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራን፣ ልዩ ልዩ አደረጃጀቶች፣ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች እና የተለያዩ ተቋማት ይሳተፋሉ ብለዋል።

የምንተክለው “ለግብር ሳይሆን ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ክብር” ነው ያሉት አቶ ኡስማን፥ ሐምሌ 10 ቀን 2015 ዓ.ም በሚከናወነው የችግኝ ተከላ የክልሉ ሕዝብ በንቃት እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።

በ2015 የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ፥ በክልሉ ከ 1 ቢሊየን በላይ ችግኝ እንደሚተከልም ነው አቶ ኡስማን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የተናገሩት።

ከመጋቢት ጀምሮም ከ530 ሚሊየን በላይን ችግኝ መተከሉን አስታውሰው፥ በቀሪው የክረምት ወቅት ከ500 ሚሊየን በላይ እንደሚተከል አመላክተዋል።

በዮሐንስ ደርበው