የሀገር ውስጥ ዜና

ሐረር ከተማ የዓለም የቅርስ ከተሞች አባል ሆነች

By ዮሐንስ ደርበው

July 12, 2023

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሐረር ከተማ ከሰሃራ በታች ካሉ ከተሞች የመጀመሪያዋ የዓለም ቅርስ ከተሞች ድርጅት አባል ከተማ ሆና ተመዘገበች፡፡

የሐረሪ ክልል ርዕሰ መተዳድር ኦርዲን በድሪ በካናዳ ኩቢክ ከተማ ሐረር የዓለም የቅርስ ከተሞች አባል ሆና የተመዘገበችበትን ፊርማ አኑረዋል።

ሐረር ከተማ 115 ሀገራትን በአባልነት በያዘው የቅርስ ከተሞች ድርጅት ውስጥ የተመዘገበችው ከፈረንጆቹ ሰኔ ወር 2023 ጀምሮ ነው።

ሐረር ከቅርስ ከተሞች መካከል አንዷ ሆና  መመዝገቧ በተማዋ ባህላዊና ታሪካዊ ቅርሶችን ለማልማት እና ለቱሪዝም ዘርፉ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተገልጿል፡፡

የቅርስ ከተሞች በጋራ ጉዳዮቻቸው ተመካክረው አቅጣጫ በማስቀመጥ ተግዳሮቶችን ለመሻገርና እድሎችን ለማስፋት ይጠቅማል መባሉን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡

ሐረር ከተማ የጁገል ዓለም አቀፍ ቅርስን ጨምሮ በተባበሩት መንግስት የሳይንስ፣ የትምህርትና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) የተመዘገቡ ዓለም አቀፍ ቅርሶች መገኛ ከተማ መሆኗ ይታወቃል፡፡

በተጨማሪም ከተማዋ ዜጎች በሰላም፣ በመቻቻልና በአብሮነት የሚኖሩባት ከተማ በሚል ዩኔስኮ እውቅና እንደተሰጣት ይታወሳል።