የሀገር ውስጥ ዜና

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር አስደናቂ እና ለበለጠ ሥራ የሚያነሳሳ ነው – የጀርመን ልዩ መልዕክተኛ

By Alemayehu Geremew

July 12, 2023

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የጀመረችው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር አስደናቂ እና ለበለጠ ሥራ የሚያነሳሳ ፕሮጀክት መሆኑን በጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ የማሻሻያ ትግበራ ልዩ መልዕክተኛ ጄኒፈር ሊ ሞርጋን ገለጹ፡፡

ልዩ መልዕክተኛዋ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ በኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ በሚል ዛፎች መተከላቸው ብቻ ሳይሆን፥ የሀገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ጨምሮ በተለያየ ደረጃ የሚገኙ አመራሮች ከሕዝቡ ጋር አብረው ችግኝ መትከላቸው ያስደንቃል ብለዋል፡፡

በአመራር ላይ ያሉት የሀገሪቱ ባለሥልጣናት ችግኝ መትከላቸው ለሕዝቡ መልካም ምሳሌ እንደሆነም ነው በቆይታቸው ያነሱት።

አያይዘውም በመርሐ ግብሩ ችግኞች በተራቆቱ ፣ በገላጣማ እና በበረሃማ አካባቢዎች መተከላቸውን አንስተዋል።

ይህም እንዴት በረሃማነትን መቋቋም እና የአፈር መከላትን መከላከል እንደሚቻል ለኅብረተሰቡ በማስተማር ረገድ መልካም ምሳሌ ይሆናልም ነው ያሉት፡፡

ልዩ መልዕክተኛዋ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ ከኢትዮጵያ ባሻገር በአፍሪካ አጠቃላይ ነባራዊ ሁኔታ ላይም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ላይ የምታሳርፈው ተፅዕኖ እዚህ ግባ የሚባል ባይሆንም እንደ ጀርመን እና ሌሎች በኢንዱስትሪ የበለጸጉ ሀገራት በሚለቁት የተበከለ አየር የተፅዕኖው ገፈት ቀማሽ ሆናለችም ነው ያሉት፡፡

በመሆኑም በኢንዱስትሪ የበለጸጉ ሀገራት በአፍሪካ ከባቢ እና የዓየር ንብረት ላይ በሚያደርሱት ብክለት ለደረሰው ጉዳት ካሳ እና ለሚያደርሱት ተፅዕኖ ማካካሻ ፈንድ መፍቀድ እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።

በዮናታን ዮሴፍ