አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የልማት ተነሺ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርገውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንስሳት ልማትና ልኅቀት ማዕከል መርቀው ከፈቱ፡፡
ማዕከሉ በ140 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ሲሆን፥ በዘርፉ ለሚሰማሩ 485 የልማት ተነሺ አርሶ አደሮችን የእውቀት፣ የክህሎት፣ የምርምር፣ የግብዓት እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ምንጭ ሆኖ ያገለግላል ተብሏል።
ማዕከሉ የልማት ተነሺዎች ለችግር እንዳይጋለጡና ወደነበሩበት የኑሮ ዘይቤ እንዲመለሱ ታስቦ የተገነባ ሲሆን፥ ከተለያዩ ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ አርሶአደሮችና የአርሶአደር ልጆች ተደራጅተው ሥራ መጀመራቸው ተገልጿል፡፡
በማዕከሉ ውስጥ አሁን በስራ ላይ ያሉ የልማት ተነሺ አርሶአደሮች ለ15 ዓመታት ከሰሩ በኋላ ራሳቸውን በማሳደግ ለሌሎች አርሶአደሮች ሼዶችን እንደሚለቁ ተጠቁሟል፡፡
ማዕከሉ የከብት ማድለብ ፣ የዶሮ እርባታ ፣ የወተት ልማት ፣ የመኖ ማቀነባበሪያ እና የገበያ አቅርቦት ዘርፎች ላይ እየሰራ መሆኑም ነው የተመለከተው፡፡
ከእንስሳት ልማት ልኅቀት ማዕከሉ በተጨማሪ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለከተማ የተገነባውን ከ70 በላይ የመሸጫ ሱቆች የተካተቱበት የአቃቂ ሰብል ምርት ገበያ ማዕከል መመረቁን ከንቲባ አዳች አቤቤ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው አስታውቀዋል፡፡
የምርት ገበያው ሱቆችን ጨምሮ መጋዘን፣ ወፍጮ ቤት እንዲሁም ልዩ ልዩ አገልግሎት የሚሰጡ ማዕከላት የተካተቱበት መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
ከንቲባዋ “የነዋሪዎቻችንን የኑሮ ጫናዎች ለማቃለል እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በታማኝነትና በትጋት መስራታችንን እንቀጥላለን” ብለዋል።
በምንተስኖት ሙሉጌታ