ዓለምአቀፋዊ ዜና

በደቡባዊ አውሮፓ ‘የሙቀት ማዕበል’ እየተስፋፋ መሆኑ ተገለፀ

By Mikias Ayele

July 13, 2023

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡባዊ አውሮፓ እና በሰሜን-ምዕራብ አፍሪካ ከፍተኛ የሙቀት መጠን እየተስፋፋ መሆኑ ተገለፀ፡፡

በቀጣዮቹ ቀናት በበርካታ የደቡባዊ የአውሮፓ ሀገራት የሙቀት መጠኑ ከ40 እስከ 48 ዲግሪ ሴሊሺየስ ይደርሳል ነው የተባለው።

በተለይም ይህ የሙቀት ማዕበል በስፔን፣ ፈረንሳይ፣ ግሪክ፣ ክሮሺያ እና ቱርክ ከ40 ዲግሪ ሴሊሺየስ በላይ ሊደርስ እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡

በጣሊያን ከተሞች የሙቀት መጠኑ እስከ 48 ነጥብ 8 ዲግሪ ሴሊሺየስ ሊደርስ እንደሚችል የተገመተ ሲሆን ፍሎረንስ እና ሮምን ጨምሮ በ10 ከተሞች ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል ነው የተባለው።

በጣሊያን በተከሰተው ከፍተኛ ሙት ምክንያት በሰሜን ጣሊያን በ40ዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ግለሰብ ራሱን ስቶ ከወደቀ በኋላ ለህልፈት መዳረጉ ተሰምቷል፡፡

‘ሴርበረስ’ የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ የሙቀት ማዕበል በእነዚህ ሀገራት ከቀጣዮቹ ቀናት ጀምሮ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚዛመትም ነው የተገለጸው።

የሙቀት ማዕበሉን ተከትሎ በሮም የሚገኙ በርካታ ጎብኚዎች ራሳቸውን ስተው እየወደቁ መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

በፈረንጆቹ 2021 በአውሮፓ ከፍተኛ የተባለው የሙቀት መጠን በጣሊያኗ ሲሲሊ ደሴት በምትገኘው ሲራከስ በተሰኘችው አካባቢ 48 ነጥብ 8 ዲግሪ ሴሊሺየስ ሆኖ መመዝገቡን ዘገባው አስታውሷል።

ባለፈው አመት ከ60 ሺህ በላይ ሰዎች ከከፍተኛ ሙቀት ጋር በተያያዘ ለህልፈት የተዳረጉ ሲሆን፥ አሁን የተከሰተው የሙቀት ማዕበል ከዚህ የባሰ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል መባሉን ባለሙያዎችን ዋቢ ያደረገው የቢቢሲ ዘገባ ያመላክታል።