የሀገር ውስጥ ዜና

የታክስና የሕግ ተገዢነት ንቅናቄ  መርሐ ግብር በጋምቤላ ክልል ተጀመረ

By Shambel Mihret

July 13, 2023

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ‘‘ግብር ለሀገር ክብር’’ በሚል መሪ ሃሳብ ክልላዊ የታክስና የሕግ ተገዢነት የንቅናቄ መርሐ ግብር በጋምቤላ ከተማ ተጀምሯል።

የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ መርሐ ግብሩን ባስጀመሩበት ወቅት እንደገለጹት÷በክልሉ ዘላቂና ቀጣይነት ያለው ልማት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩሉን ሚና ሊወጣ ይገባል፡፡

የሀገር ኢኮኖሚያዊ እድገት ቀጣይና አስተማማኝ ሊሆን የሚችለው ሃገሪቱ የምታመነጨውን የገቢ አቅም አሟጦ መሰብሰብ ሲቻል ነው ብለዋል።

መርሐ ግብሩ የግብር ከፋዩን ማህበረሰብ ግንዛቤ በማሳደግ የግብር መክፈል ባህሉን ለማሳደግ ያለመ ነው መሆኑን ገልጸዋል።

የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ ጁል ናንጋል በበኩላቸው÷በክልሉ የልማት ዕቅዶችን እውን ለማድረግ የገቢ አቅምን አሟጦ መሰብሰብ ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ ርዕሰ-መስተዳድር  ኡሞድ ኡጁሉ እና በብልፅግና ፓርቲ የፖለቲካና ርዕዮተ ዓለም ዘርፍ አስተባባሪ ሚኒስትር አቶ ዛዲግ አብርሃን ጨምሮ የክልልና የፌዴራል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች መገኘታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የንቅናቄ መርሐ ግብሩ ከሀምሌ 2015 ጀምሮ እስከ የካቲት 2016 ዓ.ም እንደየሚቆይም ተመልክቷል።