የሀገር ውስጥ ዜና

በአፋር ክልል በአንድ ጀምበር 1 ሚሊየን ችግኞች ለመትከል ዝግጅት ተደረገ

By Melaku Gedif

July 13, 2023

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፋር ክልል በአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 1 ሚሊየን ችግኞች እንደሚተከሉ የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል።

የቢሮ ሃላፊው ኢብራሂም ኡስማን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ የፊታችን ሐምሌ 10 ቀን ለሚከናወነው የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል፡፡

በመርሐ ግብሩም በክልል ደረጃ 1ሚሊየን ችግኝ ለመትከል መታቀዱን ነው የተናገሩት፡፡

ችግኞች እና የመትከያ ቦታዎች ልየታ ስራ መከናወኑን ጠቁመው ፥ ከዞን እስከ ወረዳ ያለው አመራር በቅንጅት እንዲሰራ አቅጣጫ መቀመጡንም አንስተዋል፡፡

በመርሐ ግብሩ ሀገር በቀል እና ሙቀት መቋቋም የሚችሉ የደን ተክሎች እንዲሁም የፍራፍሬ ችግኞች እንደሚተከሉ ጠቁመዋል፡፡

የክልሉ ሕዝብ በአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በንቃት እንዲሳተፍም ነው ኃላፊው ጥሪ ያቀረቡት፡፡

በበጀት ዓመቱ ከ4 ነጥብ 1 ሚሊየን በላይ ችግኝ ለመትከል ታቀዶ ወደ ስራ መገባቱንም አስታውሰዋል፡፡

በአሊ ሹምባሕሪ