የሀገር ውስጥ ዜና

በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ 3 የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሰራተኞች ፍርድ ቤት ቀረቡ

By Feven Bishaw

July 14, 2023

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ3 ሚሊየን ብር በላይ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ 3 የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሰራተኞች በቁጥጥር ስር ውለው ፍርድ ቤት ቀረቡ።

የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት የፌደራል ፖሊስ መርማሪ በግለሰቦቹ ላይ ያቀረበው የጥርጣሬ መነሻ ምክንያቶችን እና የተጠርጣሪዎችን መከራከሪያ ነጥብ ተመልክቷል።

ተጠርጣሪዎቹ ወርቅነህ መኮንን ሃይሌ፣ ወ/ት አስናቁ ዘውዴ ወርዶፋ እና አብርሃም አበራ ኢፋ ናቸው።

የፌደራል ፖሊስ መርማሪ ባቀረበው የጥርጣሬ መነሻ ምክንያቱ ላይ ተጠርጣሪዎቹ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሰራተኞች መሆናቸውን ጠቅሷል።

በዚህም 1ኛ ተጠርጣሪ በድርጅቱ ምዕራብ አዲስ አበባ ዲስትሪክት ቁጥር 4 አገልግሎት መስጪያ ማዕከል በገንዘብ ያዢነት ሲሰራ ቆይቶ በዝውውር ወደ ደቡብ አዲስ አበባ ዲስትሪክት በሌላ በስራ መደብ በተዛወረበት ወቅት ቀድሞ ይሰራበት የነበረውን የመለያ የይለፍ ቃል ለ2ኛና ለ3ኛ ተከሳሾች አሳልፎ ሰጥቷል ተብሎ የጥርጣሬ መነሻ ቀርቦበታል፡፡

2ኛ እና 3ኛ ተጠርጣሪዎች ደግሞ በሚሰሩበት የሒሳብ የመሰብሰብ ስራ ላይ ሲሰሩ ከአንደኛ ተጠርጣሪ የተቀበሉትን የይለፍ ቃል በመጠቀም ከግንቦት 14 ቀን 2015 ዓ.ም እስከ ሰኔ 1 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ ከደንበኞች የተሰበሰበ 3 ሚሊየን 524 ሺህ 300 ብር የይለፍ ቃል ተጠቅመው ገንዘቡን ለድርጅቱ ሒሳብ ማስገባት ሲኖርባቸው ሳያስገቡ ገንዘቡን ለግል ጥቅማቸው አውለዋል በሚል መነሻ መጠርጠራቸውን ፖሊስ ለችሎቱ አስረድቷል።

በተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ምርመራ ስራ አከናውኖ ለመቅረብ በወ/መ/ስ/ህ/ቁጥር 59/2 መሰረት የ14 ቀን ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል።

የአንደኛ ተጠርጣሪ ጠበቃ በበኩሉ ÷ ግለሰቡ ቅርንጫፍ ሲቀይር ድርጅቱ የይለፍ ቃል መቀየርና መዝጋት እየቻለ ይህን ባላደረገበት ሁኔታ ላይ ደንበኛዬ መለያ ቁጥር ሰጥቷል ተብሎ መጠርጠሩ ተገቢ አደለም ሲል በመከራከር የዋስ መብቱ እንዲከበር ጠይቋል።

የ2ኛና የ3ኛ ተጠርጣሪዎች ጠበቃ በኩል ደግሞ ተጠርጣሪዎቹ የራሳቸውን የይለፍ ቃል እንጂ የሌላ ተጠቅመው አልሰሩም በማለት ተከራክሯል፤ በተጨማሪም ጠበቃቸው የዋስትና ጥያቄም አቅርቧል።

መርማሪ ፖሊስ በጠበቆች በተነሱ የመከራከሪያ ነጥቦች ላይ መልስ የሰጠ ሲሆን ÷በዚህም ከደንበኞች የተሰበሰበው ገንዘብ በ2ኛ እና በ3ኛ ተጠርጣሪዎች ኮምፒዩተር መሆኑን በይለፍ ቃል፣ አይፒ በባለሙያዎች በኩል መረጋገጡን ገልጿል።

በዛ ቅርጫፍ ላይ ለ42 ቀን ተጠርጣሪዎቹ መደባቸው በሌለበት ገንዘብ ከደንበኛ ሰብስበዋል በማለት የገለጸው ፖሊስ ለዚህም የመነሻ ማስረጃ መኖሩን አስረድቷል።

የተጠርጣሪዎቹ የዋስትና ጥያቄን በመቃወም ተከራክሯል።

የግራ ቀኙን ክርክር የተከታተለው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ የአንደኛ ተጠርጣሪ በዝውውር ወደ ሌላ ቦታ ሲዛወር ድርጅቱ የይለፍ ቃሉን መቀየር ወይም መዝጋት ይገባው ነበር በማለት ተጠርጣሪውን በ20 ሺህ ብር ዋስትና ፈቅዶለታል።

የደንበኞች የተሰበሰበ ገንዘብን ለግል ጥቅም አውለዋል የተባሉ 2ኛ እና 3ኛ ተጠርጣሪዎችን በሚመለከት ግን ተጨማሪ ምርመራ መከናወን እንዳለበት በማመን የጠየቁትን የዋስትና ጥያቄ ለጊዜው ውድቅ በማድረግ ለፖሊስ 14ቀን የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ ፈቅዷል።

በታሪክ አዱኛ