የሀገር ውስጥ ዜና

በስልጤ ዞን በመሬት መሰንጠቅ አደጋ 10 አባወራዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቀሉ

By Tibebu Kebede

May 03, 2020

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 25፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በስልጤ ዞን ምስራቅ ስልጢ ወረዳ በደረሰ የመሬት መሰንጠቅ አደጋ 10 አባወራዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸው ተገለፀ።

አደጋው በዞኑ ምስራቅ ስልጢ ወረዳ ሉቄፋቃ ቀበሌ ልዩ ስሙ ደቡብ ረጤ ተብሎ በሚጠራው መንደር መከሰቱን የስልጤ ዞን ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ያደረሰን መረጃ ያመለክታል።

ትናንት አመሻሽ ላይ በተከሰተው የመሬት መሰንጠቅ ቀድሞ ከነበረው መጠኑ እየጨመረ በመሄዱ ስጋት እንደጫረባቸው የአካባቢው አርሶ አደሮች ተናግረዋል፡፡

የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሳዲቅ አህመዲን፥ የተከሰተው የመሬት መሰንጠቅ አደጋ ርዝመቱ 2 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር፤ ስፋቱ ከ29 ሜትር በላይ መሆኑን ገልፀው ጥልቀቱ እስከ 20 ሜትር የሚገመት ነው ብለዋል።

ክስተቱ ለ10 አባወራዎች ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ መንስኤ የሆነ ሲሆን፥ በሰውና በንብረት ላይ የደረሰ አደጋ አለመኖሩንም የዞኑ ስጋት ስራ አመራር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ወሲላ አሰፋ ገልፀዋል።

የስልጤ ዞን ብልፅግና ፖርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቀድሩ አብደላ፥ በአደጋው ሳቢያ የተፈናቀሉ አባወራዎችን በቀጣይ በዘላቂነት ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ የበኩሉን እንዲያደረግ ጠይቀዋል።

የዞኑ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ያሉት አቶ ቀድሩ፥ ከወራቤ ዩኒቨርሲቲና ከሌሎችም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በመሆን ክስተቱ እንዲጠና ይደረጋል ብለዋል።

የአደጋው ስፋት ለጊዜው በውል ስለማይታወቅ ነዋሪዎቹ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።