አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 3 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡን የአፋር ክልል ገቢዎች ቢሮ አስታውቋል፡፡
በቢሮው የግብር አወሳሰን ኦፊሰር መሃመድ ያዮ÷በበጀት ዓመቱ ከመደበኛ ግብር ከፋዮች እና መዘጋጃ ቤት አገልግሎት አስፈላጊውን ግብር ለመሰብሰብ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡
በበጀት ዓመቱም 3 ነጥብ 485 ቢሊየን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ 3 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡን ተናግረዋል፡፡
በዚህም የእቅዱን ከ100 በመቶ በላይ ማሳካት መቻሉን ነው አቶ መሃመድ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የገለጹት፡፡
በበጀት ዓመቱ አዳዲስ አሰራሮችን በመዘርጋት እንዲሁም ፖሊሲዎችን በማሻሻል ግብር ከፋዮች በወቅቱና በታማኝነት እንዲከፍሉ የማድረግ ስራ መከናወኑን ጠቁመዋል፡፡
ገቢው ከክልሉ ከሁሉም ከተማ አስተዳደሮች እና ወረዳዎች ከሚገኙ 15 ሺህ በላይ ግብር ከፋዮች እንደተሰበሰበ ጠቅሰዋል፡፡
ገቢው በተሳካ ሁኔታ እንዲሰበሰብ የክልሉ አመራሮች እና በየደረጃው የሚገኙ ባለሙያዎች ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን አውስተዋል፡፡
በቀጣዩ በጀት ዓመት ግብር ከፋዮች የሚጠበቅባቸውን ግብር በወቅቱ እና በታማኝነት እንዲከፍሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ