የሀገር ውስጥ ዜና

በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከ16 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር በላይ ድጋፍ አደረጉ

By Alemayehu Geremew

July 16, 2023

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከ16 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር በላይ የገንዘብ እና የዓይነት ድጋፍ አድርገዋል፡፡

ድጋፉ ለሀገራዊ ፕሮጀክቶችና ወቅታዊ ጥሪዎች የሚውል መሆኑን በአሜሪካ የኢፌዴሪ ልዩ መልዕክተኛ እና አምባሳደር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር ) (ኢ/ር) ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር መሐመድ እንድሪያስ (ዶ/ር) የተመራ ልዑክ በዋሽንግተን ዲሲ የኢፌዴሪ ኤምባሲ በመገኘት የዳያስፖራ ዲፕሎማሲና ሁለንተናዊ ተሳትፎ ላይ ከኤምባሲው ጋር ውይይት አካሄዷ።

ዳያስፖራው በግጭት ምክንያት የተጎዱ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋምና የወደሙ መሰረተ-ልማቶችን መልሶ ለመገንባት እንዲሁም ለተለያዩ አገልግሎቶች በበጀት ዓመቱ ከ965 ሺህ ዶላር በላይ በጥሬ ገንዘብና ከ15 ሚሊየን ዶላር በላይ የዓይነት ድጋፍ ማድረጉ ተገልጿል፡፡

14 የጤና እና የትምህርት ተቋማት መልሶ ግንባታ ፕሮጀክቶች በዳያስፖራው ድጋፍ መጀመራቸውም ተጠቁሟል፡፡

በተጨማሪም እስከ ግንቦት ወር 2015 ዓ.ም ባለው ጊዜ ከሰሜን አሜሪካ ብቻ ከ483 ሺህ ዶላር በላይ ወደ ሀገር ቤት በግለሰቦች “ሬምታንስ” መላኩ ተጠቅሷል፡፡

ልዑካን ቡድኑ በዋሽንግተን የሚገኘውንና የኅብረተሰብ ጤና አገልግሎት የሚሰጠውን የኢትዮጵያ ኮሙዩኒቲ ማዕከል መጎብኘቱንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡