የሀገር ውስጥ ዜና

በጋምቤላ ከተማ ደረጃውን የጠበቀ ቤተ መጽሃፍት ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ

By Alemayehu Geremew

July 16, 2023

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ከተማ ደረጃውን የጠበቀ ቤተ መጽሃፍት ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ።

የቤተ መጽሃፍቱ ግንባታ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከተጻፈው “የመደመር ትውልድ” መጽሐፍ ሽያጭ በተገኘው ገቢ ነው የሚከናወነው፡፡

የመሰረት ድንጋይ በማስቀመጥ መርሐ ግብሩ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ እና ሌሎች የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ÷ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀገር ከመምራት ከባድ ኃላፊነት ጎን ለጎን ለሀገር ግንባታ የሚጠቅሙ መጻህፍትን ማበርከታቸውን አድናቆትን የሚያስቸራቸው ነው ብለዋል።

“የመደመር ትውልድ” ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና በማሸጋገር ትልቅነቷን እንደሚያረጋግጥ ዕምነት የሚጣልበት መሆኑንም አስታውቀዋል።

በክልሉ ከ”የመደመር ትውልድ” መጽሐፍ ከ12 ሚሊየን ብር በላይ የተገኘው ገቢ ደረጃውን የጠበቀ የቤተ መጻሃፍት ግንባታ እንደሚውልም አቶ ኡሞድ ተናግረዋል።

የመደመር እሳቤ በስኬትና በፈተናዎች ውስጥ የኛ የኢትዮጵያውያን አንድነት ህብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት እህትማማችነት ጸንቶ እንዲቆም ማድረጉን ጠቁመዋል።

ግንባታው ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ድረስ የሚመለከታቸው ተጠሪ ተቋማት ለስኬታማነቱ የበኩላቸውን እንዲወጡ ማሳሰባቸውንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡