የሀገር ውስጥ ዜና

እኛ ኢትዮጵያውያን ካለብን ችግር የምንወጣው ንባብን ልክ እንደ አረንጓዴ አሻራ ዕለት በዕለት ስንተክል ነው-ጠ/ሚ ዐቢይ(ዶ/ር)

By Feven Bishaw

July 16, 2023

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)እኛ ኢትዮጵያውያን ካለብን ችግር የምንወጣው ንባብን ልክ እንደ አረንጓዴ አሻራ ዕለት በዕለት ስንተክል ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡

 

መጻሕፍት የህይወት ዘመን ጓደኛ ናቸው ሲሉም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለፁት።

 

ከተሽከርካሪ ነፃ መንገድ ያስፈልጋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ(ዶ/ር) ከሀሳብ እና ከመጻሕፍት ነፃ የሆነ ጎዳና ግን ሊኖር አይገባም ብለዋል።

 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ታነባለች ጎዳናዋም በመጻሕፍት ተሞልቶ ይትረፈረፋል ሲሉም ተናግረዋል።

 

አብርሆት ቤተመጻሕፍት ከመደበኛ ስፍራው ባለፈ በአዲስ አበባ የተለያዩ ጎዳናዎች ላይ ለታዳጊ ህፃናት መጻሕፍት ያቀርባል ደግሞም ያነባል፤ያስነብባልም ብለዋል።

 

ዛሬ መጻሕፍት የሚያነቡ ህፃናት ነገ አይሰርቁም፤ በሙስና እና በሌብነት ቀንበር ስር አይወድቁም ነው ያሉት።

 

እኛ ኢትዮጵያውያን ካለብን ችግር የምንወጣው ንባብን ልክ እንደ አረንጓዴ አሻራ ዕለት በዕለት ስንተክል ነው ሲሉም ገልፀዋል።

 

ዛሬ ለልጆች እና ለንባብ የምንሰጠው ቦታ የነገይቷን ኢትዮጵያ ፍንትው አድርጎ ያሳየናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ያላነበበ ህፃን፤ መፃህፍት የማይወድ ህፃን፤ ነገ አገር መምራትም ሆነ ብቁ ተተኪ ዜጋ መሆን አይችልም ነው ያሉት።

 

መጻሕፍት ማንበብ የመንግስት እና የፖለቲካ ጉዳይ ሳይሆን ነገ ከዓለም ጋር የምንቀመጥበት እንዲሁም ዓለምን የምናይበት መነፅር ነው ሲሉም ገልፀዋል።