የሀገር ውስጥ ዜና

በትግራይ ክልል በነገው ዕለት በአንድ ጀንበር 3 ሚሊየን ችግኝ ለመትከል ዝግጅት መደረጉ ተገለፀ

By Mikias Ayele

July 16, 2023

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል በነገው ዕለት በአንድ ጀንበር 3 ሚሊየን ችግኝ ለመትከል ዝግጅት መደረጉን  የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ግብርናና ተፈጥሮ ኃብት ቢሮ አስታወቀ።

በቢሮው የደን ልማት፣ ጥበቃና አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ ተስፋይ ተክለኃይማኖት÷ በአንድ ጀንበር 3 ሚሊየን ችግኞች በ1 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ እንደሚተከሉ ተናግረዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን በ45 ወረዳዎች የሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ-ግብር  የፌዴራል ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎችና የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮች በተገኙበት በፅራእ ወንበርታ ወረዳ በይፋ እንደሚጀመርም ተናግረዋል።

በመርሀ-ግብሩ  ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሳተፉ አመላክተዋል።

ሃላፊው በክልሉ በ64 የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች የተዘጋጁ እና ኢኮኖሚያዊ እና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ከ10 ሚሊየን በላይ ችግኞች በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ-ግብር እንደሚተከሉ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡