የሀገር ውስጥ ዜና

በክልሉ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከፍተኛ ውጤት አስገኝቷል – ርእሰ መስተዳድር ሽመልስ

By Feven Bishaw

July 17, 2023

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እስካሁን በተሰሩ ስራዎች ከፍተኛ ውጤት መገኘቱን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ፡፡

ርእሰ መስተዳድሩ እንደ ሀገር በአንድ ጀንበር 500 ሚሊየን ችግኝ የመትከል መርሐ ግብርን በክልል ደረጃ ባስጀመሩበት ወቅት ባስተላለፉት መልእክት÷ በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች በተለያየ ጊዜያት ድርቅ መከሰቱን አስታውሰዋል።

ይህም የሆነው በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት እንደሆነ ገልጸው፤ በዚህም የአየር ንብረት ለውጥ ያመጣውን ተፅዕኖ ችግኝ በመትከል ልንከላከለው ይገባል ብለዋል፡፡

በክልሉ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እስካሁን በተሰሩ ስራዎች ከፍተኛ ውጤት መገኘቱን ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በሚቀጥሉት አራት አመታት ውስጥም 20 ቢሊየን ችግኞችን በመትከል እንደሀገር የተቀመጠውን እቅድ ለማሳካት እንደሚሰራ አመልክተዋል።

ዘንድሮ በስፋት ከሚተከሉት ችግኞችም አብዛኞቹ ለምግብነት የሚውሉ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ርእሰ መስተዳድሩ “ክልላችን አረንጓዴ መሆኗን በዘፈኖቻችን ስናስተዋውቅ እንደነበረው ሁሉ በተግባርም አረንጓዴ መሆኗን ለማሳየት ተግተን እንሰራለንለ” ነው ያሉት፡፡