የሀገር ውስጥ ዜና

በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ በአንድ ጀንበር 500 ሚሊየን ችግኝ የመትከል መርሐ ግብር እየተካሄደ ነው

By Melaku Gedif

July 17, 2023

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2015(ኤፍ ቢ ሲ) በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ በአንድ ጀንበር 500 ሚሊየን ችግኝ የመትከል መርሐ ግብር እየተካሄደ ነው።

በመርሃ-ግብሩ ላይ የፕሮጀክቱ የግንባታ ሥራ ሠራተኞች እና የሀገር መከላከያ ሠራዊትና የፌዴራል ፖሊስ አባላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ክፍሌ ሆሮ (ኢ/ር) እንደተናገሩት÷ በፕሮጀክቱ ዙሪያ የሚካሄደው የችግኝ ተከላ ሥራ ግድቡን ከደለል በመከላከል ኃይል የሚያመነጭበትን እድሜ ለማራዘም ያግዛል።

ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚከናወንበት አካባቢ በደን የተሸፈነ ነው ያሉት ሥራ አስኪያጁ÷ የችግኝ ተከላ ሥራው በአካባቢው ያለውን የአረንጓዴ ልማት አስጠብቆ ለማቆየት ፋይዳው የጎላ እንደሆነ አመላክተዋል።

በፕሮጀክቱ ዙሪያ ከዚህ በፊት ሲካሄድ የነበረው የችግኝ ተከላ ሥራ በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የግድቡን ደህንነት ለማስጠበቅ ህብረተሰቡ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ላይ የሚያደርገውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥም ኢንጅነር ክፍሌ ጥሪ አቅርበዋል።

የፕሮጀክቱ ሠራተኛ የሆኑት አቶ ያሬድ ግርማ የተከላ ሥራው በግድቡ ዙሪያ መከናወኑ በተፋሰሱ ላይ የአፈር መሸርሸርን ለመከላከልና የዝናብ መጠንን ለመጨመር ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።

የዊ ቢውልድ /ሳሊኒ/ ኩባንያ ሠራተኞች ማህበር ተወካይ አቶ ሞገስ የሺዋስ በበኩላቸው ሠራተኞች በችግኝ ተከላ ሥራ ላይ እንዲሳተፉ እየተደረገ እንደሆነ ተናግረዋል።

በችግኝ ተከላው ላይ የተሳተፉት በሀገር መከላከያ ሠራዊት አባል መቶ አለቃ ድረስ ያለውና የፌዴራል ፖሊስ አባል ኮማንደር ጀማል አደም የፕሮጀክቱን ደህንነት ለማስጠበቅ እየሠሩት ካለው የሠላም ማስከበር ሥራ በተጨማሪ “ነገን ዛሬ እንትከል” በሚል ሀገራዊ ጥሪ እየተከናወነ ባለው የችግኝ ተከላ ሥራ ላይ መሳተፋቸው ትልቅ መነሳሳትን እንደፈጠረላቸው ገልፀዋል።

በዕለቱ ለምግብነት የሚውሉ ችግኞች እየተተከሉ ሲሆን ይህም በምግብ ራስን ለመቻል እየተሰራ ያለውን ሥራ በመደገፍ በኩል የራሱን አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ተመላክቷል።