አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብሩ ሕዝቡ አንድነትን በተግባር ያሳየበት መሆኑን ሐረሪ ክል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለጹ፡፡
የፌደራል እና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ከነዋሪዎች ጋር በመሆን እንደሀገር 500 ሚሊየን ችግኝ የመትከል መርሐ ግብር ላይ እየተሳተፉ ነው፡፡
የክልሉ ሕዝብ ከማለዳ ጀምሮ በነቂስ በመውጣት ዐሻራውን እያኖረ ስለመሆኑ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገልጸዋል፡፡
የተተከሉ ችግኞች እንዲፀድቁ ሕዝቡን በማሳተፍ የሚከናወነው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በበኩላቸው÷ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብሩ የሀገርን ገፅታ በማጎልበት ረገድ አስተዋጽኦው እያደረገ ስለመሆኑ አስረድተዋል፡፡
በተለይም ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለው ትስስር እንዲጠናከር ከማድረግ አንፃርም ከፍተኛ ፋይዳ አለው ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡