የሀገር ውስጥ ዜና

በሰሜን ሸዋ ዞን በደረሰ የትራፊክ አደጋ እናት እና 4 ልጆቿን ጨምሮ የ14 ሰዎች ህይወት አለፈ

By Melaku Gedif

July 17, 2023

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደገም ወረዳ አሊደሮ ቀበሌ በደረሰ የትራፊክ አደጋ እናት እና አራት ልጆቿን ጨምሮ የ14 ሰዎች ህይወት አለፈ፡፡

አደጋው እሑድ ሐምሌ 9 ቀን 2015 ዓ.ም ንጋት ላይ የአፈር ማዳበሪያ ጭኖ ከአዲስ አበባ ወደ ባህር ዳር ሲጓዝ የነበረ ተሳቢ የጭነት ተሽከርካሪ ከፊት ለፊቱ ሲጓዝ ከነበረ የሕዝብ ማመላለሽ ዶልፊን ሚኒባስ ላይ በመውጣቱ ነው የተከሰተው፡፡

በዚህም ሚኒባሱ ውስጥ የነበሩ እናት እና አራት ልጆቿን ጨምሮ የ14 ሰዎች ህይወት ማለፉን በኦሮሚያ ክልል ፖሊስ የትራፊክ አደጋ ጥናት እና ምርምር ዲቪዥን ሃላፊ ኢንስፔክተር ታደለ ሌጂሳ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡

በአደጋው ከሞቱት ሰዎች በተጨማሪ ከ3 ሚሊየን 500 ሺህ ብር በላይ የሚገመት ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ነው ሃላፊው የተናገሩት፡፡

በትራፊክ አደጋው ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ሁለት ሰዎችም አቅራቢያ በሚገኝ የጤና ተቋም የህክምና እርዳታ እያገኙ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ