የሀገር ውስጥ ዜና

አገልግሎቱ 897 ሺህ ጉዳዮችን በማስተናገድ 1 ነጥብ 77 ቢሊየን ብር ገቢ አገኘ

By Melaku Gedif

July 18, 2023

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) 897 ሺህ ጉዳዮችን በማስተናገድ ከ1 ነጥብ 77 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት አስታውቋል፡፡

የአገልግሎቱ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ስራ አስፈጻሚ አለምሸት መሸሻ እንደገለጹት÷ በ2015 በጀት ዓመት የተቀመጠውን እቅድ ከማሳካት አንጻር ስኬታማ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች 897 ሺህ 71 ጉዳዮችና 1 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ተገልጋዮችን ያለቀጠሮ ማስተናገድ መቻሉን አንስተዋል፡፡

ከተለያዩ አገልግሎት ዘርፎች 1 ነጥብ 06 ቢሊየን ብር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ 1 ነጥብ 77 ቢሊየን ብር በመሰብሰብ የዕቅዱን 167 በመቶ ማሳካት መቻሉን ነው የተናገሩት፡፡

የተሽከርካሪ ሽያጭና የብድር ውል ስምምነቶች ከፍተኛ ቁጥር መያዛቸውን የገለጹት አቶ አለምሸት÷ ይህም ከገቢው 89 ነጥብ 1 በመቶ ድርሻ ይይዛል ብለዋል።

በሐሰተኛ ሰነድ የመገልገል ወንጀል በተጠረጠሩ 121 ጉዳዮች ላይ የወንጀል ክስ ተዘጋጅቶ ለፖሊስ መቅረቡን ጠቁመው÷ ዓቃቤ ሕግም በ23ቱ ላይ ክስ መመስረቱን ተናግረዋል፡፡

1 ሺህ 733 ሃሰተኛ ማስረጃዎች ጥቅም ላይ እንዳይውሉ መደረጉን እና ከተያዙት ሃሰተኛ ማስረጃዎች ውስጥ 87 በመቶዎቹ የማንነት ማረጋገጫ መታወቂያዎች ናቸው ብለዋል፡፡

ወንጀልንን በጋራ ለመከላከል ከክልሎች፣ ከፌደራል ፖሊስ፣ ከአዲስ አበባ ፖሊስ እና ከተለያዩ የፍትሕ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ፣ ከንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ፣ ከአዲስ አበባ አሽከርካሪ ተሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ጋር በትብብር መሰራቱን አመልክተዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ