ዓለምአቀፋዊ ዜና

የአሜሪካና የቻይና የአየር ንብረት ለውጥ ትብብር ሊታደስ የሚችልበት ዕድል አለ ተባለ

By Amare Asrat

July 18, 2023

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካና የቻይና የአየር ንብረት ለውጥ ትብብር ሊታደስ የሚችልበት ዕድል እንዳለ የአሜሪካ የአየር ንብረት መልዕክተኛ ጆን ኬሪ አስታወቁ።

 

የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቀነስ አሜሪካ ከቻይና ጋር ያላትን ትብብር በመከለስ ግንኙነቱን የምታድስበት ዕድል እንደሚኖር የጠቀሱት ጆን ኬሪ፥ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የቻይና ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ጋር ተገናኝተው መምከራቸውን በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል።

 

በምክክራቸውም የካርቦን ልቀትን ጨምሮ የአየር ንብረት ቀውስን መፍታት በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ መነጋገራቸውን ጠቁመዋል።

 

ቻይና ሲደርሱ በሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኬ ያንግ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ አቀባበል የተደረገላቸው የአሜሪካ የአየር ንብረት ልዑክ ጆን ኬሪ፥ ከቻይናው አቻቸው ዢ ዤንሁአ ጋር በትናንትናው ዕለት አራት ሰዓት የፈጀ ውይይት አድርገዋል።

 

የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ሁለቱ ሀገራት በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ በትብብር መስራት እንዳለባቸው ገልጸው፥ የሚደረሱ ስምምነቶች መፈጸም እንደሚኖርባቸው ተናግረዋል።

 

የዓለም ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤቶቹ አሜሪካና ቻይና የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቀነስ በተለያየ ጊዜ ሲያደርጉት የነበረው ንግግር ካለፈው ነሐሴ ወር ጀምሮ ተቋርጦ ቆይቶ ትናንት መቀጠሉን አናዶሉ ዘግቧል።

 

ጆን ኬሪ እንደገለጹት እየጨመረ የመጣውን የዓለም የሙቀት መጠን ለመገደብ አሜሪካና ቻይና በትብብር መስራት ይጠበቅባቸዋል።