የሀገር ውስጥ ዜና

በቻይና የሚደገፈው የሥልጠና ፕሮግራም ወጣት ኢትዮጵያውያን አሽከርካሪዎችን እያበቃ ነው ተባለ

By Meseret Awoke

July 18, 2023

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቻይና የሚደገፈው የሥልጠና ፕሮግራም በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ወጣት አሽከርካሪዎችን በማብቃት ላይ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡

በቻይና የተገነባው የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር በኢትዮጵያ እና ጅቡቲ ለ55 ሺህ ዜጎች የስራ እድል መፍጠሩን የሺንዋ ዘገባ ያመላክታል።

ይህ የባቡር መስመር ከስራ እድል ፈጠራው በተጨማሪ ከ3 ሺህ ለሚበልጡ ባለሙያዎች የስልጠና እድል የሰጠ ሲሆን፥ ለኢትዮጵያ እና ጅቡቲ የባቡር ኢንዱስትሪ እድገት ጠንካራ መሰረት የጣለ መሆኑንም ዘገባው አመላክቷል።

በዚህ ዕድል ተጠቃሚ ከሆኑን አንደኛው ደጀን ይገዙ ይባላል፡፡

በኢትዮጵያ በኤሌክትሪክ የሚንቀሳቀሱ ባቡሮች መንጃ ፍቃድ ከወሰዱት መካከል አንደኛው ሲሆን፥ በቻይና የተገነባውን የኢትዮ-ጅቡቲ ደረጃ መለኪያ የባቡር መስመር በአስተማማኝ ሁኔታ የማሽከርከር እና ታዳጊ ወጣቶችን የማሰልጠን ሁለት ኃላፊነት እንደተሰጠው ይናገራል።

የባቡር ካፒቴን አሰልጣኝ ብቻ እንደነበር የሚያነሳው ደጀን ይህን እድል በቻይናውያን በመሰልጠን ማግኘቱን ይገልጻል።

በአሁኑ ወቅት ግን ስልጠናውን ለሌሎች ሰልጣኞች እየሰጠ መሆኑን በመጥቀስም “የራሳችንን ባለሙያዎች ማብቃት እንችላለን” ሲልም ይገልጻል፡፡

ቻይና ለኢትዮጵያ የባቡር መሰረተ ልማት ከመገንባት ጀምሮ የአካባቢውን ነዋሪዎች በባቡር ኦፕሬሽን ዕውቀትና ክህሎት ለማብቃት የምታደርገው ድጋፍም የሚደነቅ መሆኑንም ነው ያነሳው፡፡

752 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የኢትዮ ጅቡቲ ደረጃ መለኪያ የባቡር መስመር የአዲስ አበባ-ጅቡቲ የባቡር መስመር ተብሎም ይጠራል፡፡

በአፍሪካ የመጀመሪያው በኤሌክትሪክ የሚሰራ ድንበር ተሻጋሪ የባቡር መስመር እንደሆነም ነው ዘገባው የሚያመላክተው፡፡

የባቡር መስመሩ ከሦስት ቀናት በላይ የነበረውን የእቃ ማጓጓዣ ጊዜን ወደ 20 ሰዓት ዝቅ በማድረግ የባህር በር የሌላት ኢትዮጵያን የገቢና ወጪ ምርቶቿን በቀላሉ እንድታስገባና እንድትልክ ማድረግ መቻሉም ይጠቀሳል።