የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዲፕሎማሲ ስራ ዓለም አቀፍ ተቀባይነትን እያገኘ መጥቷል – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

By Melaku Gedif

July 19, 2023

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዲፕሎማሲ ስራ ዓለም አቀፍ ተቀባይነትን እያገኘ መጥቷል – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዲፕሎማሲ ስራ ዓለም አቀፍ ተቀባይነትን እያገኘ መምጣቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር መለሰ አለም በውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሳምንታዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው÷ በአረንጓዴ አሻራ በአንድ ጀምበር ከ566 ሚሊየን በላይ ችግኞችን በመትከል በሀገር አቀፍ ደረጃ ታሪክ ተሰርቷል ብለዋል።

በዚህ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት ተሳትፎ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

በመላው ዓለም የሚገኙ የኢትዮጵያ ሚሲዮኖችም በያሉበት በዚህ ተግባር ላይ መሳተፋቸውን ነው ያመላከቱት፡፡

የአረንጓዴ አሻራ ለአፍሪካ ብቻ ሳይሆን ለዓለም አርአያ የሚሆን ነው ያሉት አምባሳደር መለስ÷ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዲፕሎማሲ ስራ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እያገኘ መምጣቱን ገልጸዋል።

የአረንጓዴ አሻራ ከኢትዮጵያ አልፎ አሁን ላይ የአፍሪካ ፕሮግራም ሆኗል ነው ያሉት ቃል አቀባዩ።

የኢትዮጵያን አረንጓዴ ታሪክ የመጻፍና የማስቀመጥ ስራ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የበኩሉን ኃላፊነት ይወጣል ብለዋል፡፡

ሚኒስቴሩ በዚህ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ለተሳተፉ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት ምስጋናውን አቅርቧል።