የሀገር ውስጥ ዜና

አምባሳደር ተስፋዬ ይታይህ ከእስራኤል ፓርላማ አባል ጋር ተወያዩ

By Mikias Ayele

July 19, 2023

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በእስራኤል የኢትዮጵያ አምባሳደር ተስፋዬ ይታይህ ከእስራኤል ፓርላማ አባል (ክኔሴት) ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡

ኢትዮጵያ እና እስራኤል ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ ታሪካዊ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዳላቸው በውይይቱ ላይ የጠቀሱት አምባሳደር ተስፋዬ፤ ሀገራቱ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በግብርና፣ ትምህርት መስኮች በትብብር እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

ትብብሩን ማስፋት እንደሚያስፈልግም አስረድተዋል፡፡

የእስራኤል ፓርላማ አባል አቶ ሞሼ ሰለሞን በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና በእስራኤል ክኔሴት መካከል የፓርላማ ወዳጅነት መመስረት እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል፡፡

በሀገራቱ መካከል የቢዝነስ ትስስርን ከማጎልበት አንጻር በርከት ያሉ ቤተ-እስራኤላውያን ወጣቶች መኖራቸው እንደ እድል የሚነሳ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በውይይቱ በአጠቃላይ የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት በተመለከተ ፣በጦርነት ወቅት የተጎዱ አከባቢዎች ላይ እየተሰሩ ያሉ  የመልሶ ግንባታ ስራዎች እንዲሁም ሌሎች  ወቅታዊ ሁኔታዎችን በተመለከተ ምክክር አድርገዋል፡፡