የሀገር ውስጥ ዜና

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል 13 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በጀት ፀደቀ

By Shambel Mihret

July 19, 2023

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት ለ2016 በጀት ዓመት 13 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በአብላጫ ድምጽ አጸደቀ።

በክልሉ የበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለ2016 ዓ.ም በጀት አመት የቀረበውን 13 ቢሊየን 528 ሚሊየን 743 ሺህ 144 ብር ነው ምክር ቤቱ ያፀደቀው፡፡

6 ነጥብ 44 ቢሊየን ከፌደራል መንግስት በድጎማ የሚገኝ፣ 6 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ከውስጥ ገቢ፣434 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር ለዘላቂ ልማት ግቦች እና 40 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ከዕርዳታ እንደሚገኝ ተጠቅሷል፡፡

ከቀረበው በጀት ለዞኖች 10 ነጥብ 8 ቢሊየን፣ ለክልሉ ማዕከል መደበኛና ካፒታል ወጪ 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር እንዲሁም ለክልላዊ ፕሮግራሞች 722 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር በጀት እንደተያዘ ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም ለዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈጸሚያ 434 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር፣ ለክልሉ መጠባበቂያ 100 ሚሊየን ብር እንዲሆን መደልደሉን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡