አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሚቀጥሉት አስር አንድ ቀናት የዝናቡ ስርጭቱ በተሻለ ሁኔታ የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎችን እንደሚሸፍን የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
በሚቀጥሉት አሥራ አንድ ቀናት ዝናብ ሰጭ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች በሰሜን ምስራቅ እና በምስራቅ የሀገሪቱ ሥፍራዎች ካለፉት አስር ቀናት አኳያ በአንፃራዊነት የመዳከም አዝማሚያ ሊኖር እንደሚችል የትንበያ መረጃዎች ይጠቁማሉ::
ከዚሁም ጋር ተያይዞ በሚቀጥሉት አሥራ አንድ ቀናት በሰሜን ምስራቅና ምስራቅ የሀገሪቱ ሥፍራዎች ዝናቡ በመጠንም ሆነ በሥርጭት የመዳከም አዝማሚያ እንደሚኖረው ከኢንቲትዩቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ይሁን እንጂ አልፎ አልፎ ከሚጠናከሩት የደመና ክምችቶች ላይ በመነሳት በተለይም በመካከለኛዉ፣ በደቡብ ምዕራብና በምዕራብ የሃገሪቱ ቦታዎች ላይ ከሚጠናከሩ የደመና ክምችቶች ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን ያለዉ ዝናብ እንደሚኖራቸው የአሃዛዊ ትንበያ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
በዚህም መሰረት ከኦሮሚያ ክልል ጅማ፣ ኢሉአባቦራ፣ ምዕራብ፤ ምስራቅ እና ቄለም ወለጋ፣ ሆሮ ጉዱሩ፣ አርሲ እና ምዕራብ አርሲ፣ ሁሉም የሸዋ ዞኖች፣ ከአማራ ክልል ምዕራብና ምሥራቅ ጎጃም፣ የሰሜንና የደቡብ ጎንደር፣ ባህር ዳር ዙሪያ፣ አዊ ዞን፣ ሸዋ፣ የደቡብ ወሎ ዞኖች እንዲሁም አዲስ አበባ፤ በአብዛኛው ከመደበኛው ጋር የተቀራረበና አልፎ አልፎም በአንዳንድ ቦታዎቻቸው ከሚጠናከሩ የደመና ክምችቶች በጥቂት ሥፍራዎች ላይ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖር ተገልጿል፡፡
የጋምቤላና የቤንሻንጉል ክልል ዞኖች፤ ከደቡብ ክልል የጉራጌ፣ የስልጤ፣ የሀዲያ፣ ከንባታ፣ ሀላባ፤ የወላይታ፣ የየም፤ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የከፋ፣ የሸካ፣ የኮንታ፣ የዳውሮ ዞኖች፤ በአብዛኛው ከመደበኛው ጋር የተቀራረበና አልፎ አልፎም በአንዳንድ ቦታዎቻቸው ከሚጠናከሩ የደመና ክምችቶች በጥቂት ሥፍራዎች ላይ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖር አሀዛዊ የትንበያ መረጃዎች ያመላክታሉ።
በተጨማሪም ጥቂት የባሌ ዞን፣ ምዕራብና የምሥራቅ ሐረርጌ፣ ድሬዳዋና ሐረሪ፣ የጅጅጋ፣ የሲቲና የፋፈን ዞኖች፤ የጋሞ፤ የጎፋ ዞኖች፤ የሲዳማ ክልል ዞኖች፤ ሁሉም የትግራይ ዞኖች፤ ዋግ ህምራ፣ የሰሜን ወሎ ዞኖች፤ ከአፋር ክልል ዞን 3 እና 5 በጥቂት ሥፍራዎቻቸው ላይ አነስተኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ የትንበያ መረጃዎች ያሳያሉ።
በሌላ በኩል የጌዲዮ፣ ደቡብ ኦሞና የሰገን ሕዝቦች፤ የቤንች ማጂ፤ ከአፋር ክልል ዞን 1፣2 እና 4፤ ከኦሮሚያ ክልል ቦረና እና ጉጂ፤ ከሶማሌ ክልል ሊበን፣ አፍዴር፣ ሸበሌ፣ ቆራሂ፣ ኖጎቦ እና ዶሎ ዞኖች ግን አልፎ አልፎ ከሚኖራቸው አነስተኛ የደመና ሽፋን በስተቀር በአብዛኛው ደረቅ ሆነው ይቆያሉ ነው የተባለው።