አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ንግድና ከአገር አቀፍ የመንግስትና የግል ዘርፍ ጋር የሚመክር መድረክ ሊካሄድ ነው።
የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት በ 3 ወሳኝ የግሉ ዘርፍ አጀንዳዎች ላይ ዛሬ በሰጠው መግለጫ በተለያዩ ዘርፎች ላይ የሚታዩ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የሚያስችል የመንግስትና የግል ዘርፍ ምክክር እንደሚካሄድ አመልክቷል።
የምክክሩ ዋና ዓላማ በአገሪቱ የኢኮኖሚ ብዝሀነትና የስራ ፈጠራ ወሳኝ ሚና ያላቸውን የግብርና፣ የቱሪዝምና የኢ-ኮሜርስ ዘርፎች ላይ የሚስተዋሉ ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ያለመ እንደሆነ ተገልጿል።
ምክክሩ የሚዘጋጀው በንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የጋራ ትብብር ሲሆን በፓን አፍሪካ የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት የቴክኒክ ድጋፍ እንዲሁም የስዊድን ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ የገንዘብ ድጋፍ አማካኝነት እንደሆነ በመግለጫው ተጠቅሷል።
በተጨማሪም የንግዱ ማህበረሰብ አባላት፣ የፖሊሲ አውጪዎችና ሌሎች የሚለከታቸው ባለድርሻ አካላት የሀሳብ ልውውጥ እንዲያደርጉ፣ አዋኪ የቁጥጥር ጉዳዮች እንዲፈቱ፣ ኢኮኖሚያዊ እድገትና ልማትን ለማስፋፋት አዳዲስ መፍትሄዎችን እንዲያፈላልጉ እድል የሚከፍት እንደሆነም ነው በመግለጫው የተመላከተው።
የመድረኩ ተሳታፊዎች ገንቢ ምክክር በማድረግ የእነዚህን የኢኮኖሚ ዘርፎች በሙሉ አቅም የሚያሰሩ ተግባራዊ ስልቶችና የፖሊሲ አቅጣጫዎች ላይ ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የምክክር መድረኩ ሐምሌ 18 እና 19 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ምክር ቤቱ ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።