የሀገር ውስጥ ዜና

በመዲናዋ በጫኝና አውራጅነት የተሰማሩ ግለሰቦች መመሪያ ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑ ተገለጸ

By Meseret Awoke

July 22, 2023

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በመዲናዋ በጫኝና አውራጅነት የተሰማሩ ግለሰቦች የሚተዳደሩበት መመሪያ ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ገለጸ።

የአዲስ አበባ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ እና የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን በ2015 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም እና በ2016 በጀት ዓመት እቅድ ላይ ተወያይቷል።

የአዲስ አበባ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ሊዲያ ግርማ እንደገለጹት ፥ በ2015 ዓ.ም የማኅበረሰቡ የመልካም አስተዳደር ችግር የሆኑ ጉዳዮችን በመለየት መፍትሔ ለመስጠት ወደ ሥራ ተገብቷል።

በመዲናዋ አንዳንድ በጫኝና አውራጅነት የተሰማሩ አካላት ከተደራጁበት ዓላማ ውጭ በመንቀሳቀስ ለኅብረተሰቡ ሥጋት ሲሆኑ መስተዋሉንም ነው ያነሱት።

በእነዚሁ አካላት ላይ በተወሰደ እርምጃ ከ5 ሺህ 46 በላይ የሚሆኑ ማኅበራትን የማፍረስ ሥራ መሠራቱን ጠቁመዋል።

ለማኅበረሰቡ ግልጋሎት የሚሰጡ የጫኝና አውራጅ አደረጃጀቶች በቢሮው በኩል በአዲስ መልክ እየተደራጁ መሆኑንም ነው የገለጹት።

በቅርቡም የሕግ ማዕቀፍ እንዲኖራቸው የሚያደርግና የሚተዳደሩበት መመሪያን ለኅብረተሰቡ ይፋ እንደሚደረግ አመላክተዋል።

በሂደትም ከመደበኛ ሥራዎቻቸው ጎን ለጎን ከጸጥታ አካላት ጋር በጋራ የሚሰሩበት መንገድ እንደሚኖርም ነው የተናገሩት።

ከባጃጅ ተሽከርካሪዎች ጋር በተያያዘ በሌብነትና ሕገ-ወጥ ተግባራት ላይ የተሰማሩና ከታሪፍ በላይ ክፍያ በመጠየቅ ማኅበረሰቡ ላይ ሥጋት የፈጠሩ አሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል በከተማዋ ሕገ-ወጥ ድርጊት እንዳይስፋፋ የሚያደርጉ ሌሎች እርምጃዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውንም ተናግረዋል።

በቀጣይም ኅብረተሰቡንና የሰላም ሰራዊቱን ያሳተፉ የፀጥታ ሥራዎች ተጠናከረው እንደሚቀጥሉም ነው የቢሮ ኃላፊዋ የተናገሩት።

በ2016 በጀት ዓመት መልካም ተሞክሮዎችን በማስፋት መሰረታዊ የሰላምና ጸጥታ ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት እንደሚሰራ መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።