የሀገር ውስጥ ዜና

በክልሎችና በከተማ መስተዳድሮች የመስክ ምልከታ ያደረገው የፌዴራል ከፍተኛ አመራሮች ቡድን በግኝቶቹ ላይ ተወያየ

By Meseret Awoke

July 22, 2023

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በ10 ክልሎች እና በሁለቱ ከተማ መስተዳድሮች ለ10 ቀናት የክትትልና ድጋፍ የመስክ ምልከታ ያደረገው የፌዴራል ከፍተኛ አመራሮች ቡድን በዋና ዋና ግኝቶቹ ላይ የጋራ ውይይት አካሄደ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በተካሄደው ውይይት ከተለያዩ ዘርፎች ተሰባጥሮ ከትግራይ ክልል በስተቀር በሁሉም የሀገሪቱ አቅጣጫ የተጓዘው የአመራር ቡድን በምልከታው ያሰባሰበውን መልካም ተሞክሮ እና ችግሮችን አቅርቧል።

ቡድኑ በዋናነት ምልከታውን ያካሄደው በሁሉም አካባቢዎች በክረምት በጎ ፈቃድ፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ በሌማት ትሩፋት ፣ በመኸር ግብርና ፣ በገበታ ለትውልድ፣ በመንግሥት ገቢ አሰባሰብ፣ በኤክስፖርት አፈጻጸም ፣ በስራ እድል ፈጠራ እና የኑሮ ውድነት ቅነሳ ፣ በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ ፣ በአመራር አቅም ግንባታ እንዲሁም በጸጥታ ኃይል ሪፎርም ስራዎች ላይ ነው።

የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት እና የጽ/ቤት ሀላፊ አቶ አደም ፋራህ እንደገለጹት ፥ የክትትልና ድጋፉ ዓላማ እያንዳንዱ ስራ ያለበትን ደረጃ በመለየት መልካሙ ተሞክሮዎች የሚሰፉበትን ጉድለቶች የሚሞሉበትን መንገድ መለየት ነው።

በተጨማሪም በፌዴራል መንግስት እና በክልሎች እንዲሁም ከተማ መስተዳድሮች የበለጠ መቀናጀት እንዲፈጠር ማስቻል ነው ብለዋል።

ቡድኑ በምልከታው በሁሉም ዘርፍ በሀገር አቀፍ ደረጃ መልካም ጅምሮች መኖራቸውን አረጋግጧል።

ሆኖም ከዜጎች ፍላጎት እና ከሀገራዊ አቅም አንጻር አፈጻጸሙን በስፋት እና በጥራት ማሳደግ እንደሚገባም አመላክተዋል።

በአልዓዛር ታደለ