የሀገር ውስጥ ዜና

የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት እንዲሳካ አስተዋጽዖ ላደረጉ የአፍሪካ ህብረት የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላምና ደህንነት ኮሚሽን ዕውቅና ተሰጠ

By Shambel Mihret

July 22, 2023

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፕሪቶሪያው ሰላም ስምምነት እንዲሳካ አስተዋጽዖ ላደረጉ የአፍሪካ ህብረት የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላም እና ደህንነት ኮሚሽን እንዲሁም ቡድን የእውቅና መርሐ ግብር አካሄደ።

የኢፌዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በቅርቡ አፍሪካ ህብረት ላደረገው አስተዋጽዖ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ የሰጠችውን እውቅና አስታውሰዋል፡፡

በዛሬው ዕለትም በአፍሪካ ኅብረት ለሚመራው የሰላም ሂደት እና የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ስኬት ለፖለቲካ ጉዳዮች፣ ሰላምና ደህንነት አመራር እና ቡድኑ ላበረከቱት አስተዋጽኦ የእውቅና ሰርተፍኬት ተሰጥቷል።

በስምምነቱ ወቅት የተደረሰው ስምምነት አፈፃፀም ቀጣይነት ያለው እድገት እያስመዘገበ መሆኑንና ለተሟላና ወቅታዊ ትግበራም መንግስት ቁርጠኛ መሆኑንም አቶ ደመቀ ተናግረዋል።

በአፍሪካ ህብረት ድጋፍና አስተዋፅዖ ቀሪ ሥራዎች ተግባራዊ እንደሚሆኑም ነው ያነሱት።

የፖለቲካ ጉዳዮች፣ሰላምና ፀጥታ ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዲኦዬ በበኩላቸው፥ ለፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ስኬት እውቅና በማግኘታቸው አመስግነዋል።

በአንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት ያሉ ግጭቶች ከኢትዮጵያ ልምድ በመውሰድ ወደመፍትሔ መምጣት እንደሚቻል መማር ይነኖርባቸዋልም ብለዋል።