የሀገር ውስጥ ዜና

ተሰርቀው የተከማቹ  የመሰረተ ልማት ገመዶች በቁጥጥር ስር ዋሉ

By Mikias Ayele

July 24, 2023

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከተለያዩ ተቋማት ተሰርቀው የተከማቹ በርካታ የመሰረተ ልማት ገመዶች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡

ፖሊስ በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 በተለምዶ ላቦራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ጥናት እና ክትትል በማድረግ በህግ አግባብ ባከናወነው ብርበራ ለመሰረተ ልማት ዝርጋታ የሚውሉ በርካታ ገመዶችን በቁጥጥር ስር አውሏል፡፡

ከወንጀሉ ጋር በተያያዘ የተጠረጠረ አንድ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ውሎ ምርምራ እየተደረገበት መሆኑን ፖሊስ ገልጿል፡፡

ከተያዙት ገመዶች መካከል ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን፣ ኢትዮ ቴሌኮም እና ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ተቋማት የሚገለገሉባቸው ንብረቶች እንደሚገኙበት ታውቋል፡፡

ህብረተሰቡ የተሰረቁ የመሰረተ ልማት ዕቃዎችን ባለመግዛትም ሆነ  በእነሱ ላይ በሚፈፀሙ ወንጀሎች ዙሪያ የሚኖረውን መረጃ በመስጠት የድርሻውን እንዲወጣ ፖሊስ መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡