አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል ተፈጽሟል ከተባለ የንፁሀን ዜጎች ግድያ ጋር ተያይዞ የተከሰሱ የክልሉ የቀድሞ የፖሊስ ኮሚሽነሮችና የልዩ ኃይል አዛዦችን ጨምሮ በ15 ተከሳሾች ላይ ምስክር ለመስማት ተቀጠረ።
ምስክር ለመስማት የተቀጠረው ተከሳሾቹ ወንጀሉን አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው የዕምነት ክህደት ቃላቸውን መስጠታቸው ተከትሎ ነው።
ምስክር ለመስማት ተለዋጭ ቀጠሮ የሰጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የፀረ ሽብርና ህገመንግስታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።
ተከሳሾቹ የቀድሞ የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር አቡላ ኦባንግ፣ ም/ኮሚሽነር የነበሩት ቱት ኮር፣ የክልሉ የልዩ ኃይል ዋና አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር ኮንግ ሬክ እና የክልሉ ልዩ ኃይል ምክትል አዛዥ የነበሩት ዋና ኢንስፔክተር ኡጀዲ ባሬን እና የተለያዩ የፀጥታ አባላቶችን ጨምሮ አጠቃላይ 15 ናቸው።
ከተከሳሾች መካከል ከ1ኛ እስከ 13ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾች ከማረሚያ ቤት ቀርበው ጉዳያቸውን በችሎት ተከታትለዋል።
በጋምቤላ ከተማ በሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም የሸኔ ሽብር ቡድን እና የጋምቤላ ነጻ አውጪ ፓርቲ (ጋነግ) በጋራ በመሆን በጋምቤላ ከተማ በቀበሌ 03 በኩል በፌደራል ፖሊስ ካምፕ እና በክልሉ ልዩ ኃይል እንዲሁም በሌሎች ፀጥታ አካላት ላይ የከፈቱትን ድንገተኛ ተኩስ ተከትሎ በወቅቱ በፀጥታ ኃይሎች የሽብር ቡድኑ ወደ መጣበት እንዲመለስ ከተደረገ በኋላ ማንነታቸው የተለዩ 35 ሰዎች እና ማንነታቸው ያልተለዩ በርካታ ንፁሃን ዜጎችን መረጃ ሰጥታችኋል በሚል ምክንያት በአሰቃቂ ሁኔታ እንዲገደሉ ትዕዛዝ በመስጠትና በመግደል ተሳትፎ ተጠርጥረው ክስ እንደተመሰረተባቸው ይታወሳል።
በጦርነት ጊዜ ንፁሃን ሰዎችን ለመጠበቅ ሲባል የወጣውን የጄኔቫ ቃል ስምምነት የፕሮቶኮል ድንጋጌን በመለተላለፍ እንዲሁም በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢፌዴሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 32/1 ሀ1/ለ፣ አንቀጽ 35 እና አንቀጽ 270 /ሀ ስር የተደነገጉ ድንጋጌዎችን በመተላለፍ ወንጀል ነው ክስ የተመሰረተባቸው።
የተመሰረተባቸው ክስ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊትን እንደፈጸሙና እንዳልፈጸሙ በችሎት ተጠይቀው፤ ከአስራ ሶስቱም ተከሳሾች በክሱ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አልፈጸምንም ወንጀለኛ አደለንም በማለት የዕምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል።
ዐቃቢህግ በበኩሉ ተከሳሾቹ ወንጀሉን አልፈጸምንም ብለው ክደው የተከራከከሩ መሆኑ ጠቅሶ ለወንጀሉ መፈጸም የሚያስረዱ ምስክሮች ቀርበው እንዲሰሙለት ጠይቋል።
ፍርድ ቤቱም የዐቃቢህግ ምስክሮችን ለመስማት ከሐምሌ 24 ቀን እስከ ሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
ቀጠሮውን በሚመለከት ዐቃቢ ህግ ከጋምቤላ የሚቀርቡ ምስክሮችን ለማምጣት ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር በአጭር ጊዜ ለማቅረብ እንደሚቸገር ገልጾ ቀጠሮው እንዲራዘምለት ጠይቋል።
በተከሳሾቹ በኩል ግን የተሰጠው የቀጠሮ ጊዜ እንዲፀናላቸው ጠይቀዋል።
በዚህ ጊዜ ዐቃቢህግ ”ምስክሮችን ለማምጣት ብንቸገር እንኳ ምስክር አላቀረባችሁም ተብለን መዝገቡ ቢቋረጥ በይግባኝ መከራከር እንድንችል ከወዲሁ የጠየቅነው የይራዘምልን ጥያቄ ይመዝገብልን” በማለት አመልክቷል።
በችሎቱ ዳኞች በኩል የመደበኛ ችሎት ያለው ጊዜ እስከ ሐምሌ 30 መሆኑን ተከትሎ እንዲሁም የተከሳሾችን የተፋጠነ ፍትህ የማግኘት መብትን ታሳቢ በማድረግ በተሰጠው ቀጠሮ ብቻ ምስክሮችን ለመስማት እንደሚችል ማብራሪያ ተሰጥቶ የቀጠሮ ለውጥ እንደማይደረግ ተገልጿል።
በታሪክ አዱኛ