አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ በቡኖ በደሌ ዞን የሩዝ ልማት መርሐ ግብርን በይፋ አስጀምረዋል።
በተያዘው የክረምት ወቅት በቡኖ በደሌ ዞን ሰባት ወረዳዎች 114 ሺህ ሄክታር መሬት በሩዝ ምርት የሚሸፈን ሲሆን÷ ከ6 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ተገልጿል።
መርሐ ግብሩ በይፋ በተጀመረበት ወቅት በበደሌ ወረዳ ቆሎሲሪ ቀበሌ ላይ ከ6 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት በሩዝ ምርት እንደሚሸፈን ተጠቅሷል።
በክልሉ የሩዝ ምርትን በብዛት እና በጥራት በማምረት ከውጪ የሚገባውን ምርት በሀገር ውስጥ ለመተካት እንደሚሰራም ተጠቁሟል።
አርሶ አደሮች በበኩላቸው÷ ከሩዝ ልማት ተጠቃሚ ለመሆን አስፈላጊ ዝግጅት እንዳደረጉ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ፣ የክልሉ ግብርና ቢሮ ሃላፊና ሌሎች የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።