አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በእነ መላክ ምሳሌ መዝገብ በሽብር ወንጀል ዝግጅት ከተከሰሱ 20 ግለሰቦች መካከል 19ኙ ያቀረቡት የዋስትና ጥያቄ ውድቅ ተደርጓል፡፡
የዋስትና ጥያቄው ውድቅ የተደረገውም ከቀረበባቸው የሽብር ክስ ውስብስብነት አንጻር ቢወጡ የዋስትና ግዴታቸውን አክብረው ሊቀርቡ ይችላሉ የሚል ግምት በፍርድ ቤቱ ባለመያዙ ምክንያት መሆኑ ተመላክቷል፡፡
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የፀረሽብርና የሕገ-መንግስት ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው ዛሬ ከሰዓት በኋላ በዋለው ችሎት ብይኑን የሰጠው ።
ዐቃቤ ሕግ ተከሳሾቹ ላይ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ዓላማን ለማሳካት በአካል በመገናኘት በመደራጀትና በመወያየት እንዲሁም በመጋቢት ወር 2015 ዓ.ም በዋትስአፕ የበይነመረብ መገናኛ ዘዴ ላይ ዕቁብ የሚል ስም የተሰጠው መወያያ በመክፈት በጋራ በቡድን በመወያየት፣ የአማራ ብልፅግና፣ ህወሓትና የኦሮሞ ብልፅግና ጠላቶቻችን ስለሆኑ በሃይል እርምጃ መጥፋት አለባቸው የሚል ስምምነት በማድረግ ፣አምስቱ የአማራ አናብስቶች ንቅናቄ የተባለ ህቡዕ ድርጅት መመስረት፣ ለድርጅቱ ፋይናንስ ማፈላለግ እንዲሁም የሃይል ጥቃት የሚጀመርበት ስፍራዎችን በመምረጥ የሽብር ወንጀል ለመፈፀም ዝግጅት አድረገዋል በማለት በሰኔ 20 ቀን 2015 ዓ.ም የሽብር ወንጀል ክስ መመስረቱ ይታወሳል።
በክሱ ላይ በአዲስ አበባ ከተማ ሕዝባዊ አመፅ ለማስነሳት በመዘጋጀት፣ በሕዝባዊ አመፁ ወደ ቤተ መንግስት አቅጣጫ በሚታለፍበት አካባቢ ባሉ ፖሊስ ጣቢያዎች ፣ ነዳጅ ማደያዎች እና የመንግስት ተቋማትን ማቃጠል ጉዳት እንዲደርስ እንዲደረግ እና በዚህም መንግስት መከላከል እንዳይችል አቅጣጫ በማስቀመጥ መስማማት እና እንደአጠቃላይ ለሽብር ተግባር መዘጋጀት የሚሉ ዝርዝሮች በክሱ ጭብጥ ላይ ተካተዋል።
እንደ አጠቃላይ ሚያዝያ 23 ቀን 2015 ዓ.ም በግምት ከቀኑ 8 ሰዓት ሲሆን አዲስ አበባ መገናኛ አካባቢ መተባበር ህንጻ 4ኛ ፎቅ ላይ የህቡዕ አደረጃጀት አባላትና አመራሮች ሕዝባዊ አመፅ ማስነሳትን መሰረት ያደረገ ስብሰባ በማካሄድ፣ የውሃ ልክ፣ አሸዋ፣ ሲሚንቶ፣ ግንበኛ፣ የሚል መጠሪያ ኮድ በመሰጣጠት፣ ገንዘብ ማሰባሰብ፣ የጦር መሳሪያ እና ለወታደራዊ ምግብ ግዢ ለማዋል መዘጋጀት፣ ሕዝቡን ለማሸበርና መንግስትን ለማስገደድ በማሰብ የሽብር ድርጊት ለመፈጸም ዝግጅት ማድረግ የሚሉ ነጥቦችን ዐቃቤ ሕግ በክሱ ላይ ጠቅሶ የተሳትፎ ደረጃ ተካቶ የቀረበው ክስ በችሎቱ በንባብ ተሰምቶ ነበር።
ይህ የክስ ዝርዝር በችሎት ከተሰማ በኃላ በተከሳሽ ጠበቆች በኩል በተከሳሾች ላይ የቀረበው የሽብር ወንጀል አንቀጽ ዋስትና እንደማያስከለክል በመግለፅ ፣ተከሳሾቹ ቋሚ አድራሻ እንዳላቸው፣የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቸውን እንዲሁም የማህበራዊ ኃላፊነት ያላቸውና የሕግ ግዴታቸውን አክብረው እንደሚቀርቡ ጠቅሰው የዋስትና መብታቸው እንዲከበር ፍርድ ቤቱን ጠይቀው ነበር።
በዐቃቤ ሕግ በኩል ደግሞ ተከሳሾቹ ቋሚ አድራሻ እንደሌላቸው በመግለጽ፣ በኮድ ስም በመያዝ ለሽብር ተግባር ዝግጅት በማድረግ ሲንቀሳቀሱ ነበር በማለት በዋስ ቢወጡ በስራቸው ካደራጇቸው ቡድኖች ጋር በመቀላቀል የተዘጋጁትን የሽብር ተግባር ሊያስቀጥሉ ይችላሉ በማለት ዐቃቤ ሕግ የዋስትና ጥያቄያቸውን በመቃወም መከራከሩ ይታወሳል።
እንደ አጠቃላይ የተከሳሾቹን የዋስትና መብትን በሚመለከት የግራ ቀኝ ክርክሮችን የተከታተለው ችሎቱ መርምሮ ብይን ለመስጠት ለዛሬ በያዘው ተለዋጭ ቀጠሮ መሰረት መርምሮ በተከሳሾች ጠበቆች የተነሱ አጠቃላይ የዋስትና የመከራከሪያ ነጥቦች አለመቀበሉን አስታውቋል።
ፍርድ ቤቱ የተከሳች ጠበቆች ያቀረቡት የዋስትና መከራከሪያ ነጥብን ያልተቀበለበት ምክንያት አብራርቷል።
በዚህም 19 ተከሳሾች ላይ ከቀረበባቸው የሽብር ክስ ውስብስብነት አንጻር ቢወጡ የዋስትና ግዴታቸውን አክብረው ሊቀርቡ ይችላሉ የሚል ግምት በፍ/ቤቱ ባለመያዙ ምክንያት መሆኑን ተጠቅሶ የዋስትና ጥያቄያቸው በሙሉ ድምጽ ውድቅ ተደርጓል።
በሌላ በኩል ፍርድ ቤቱ በዚሁ መዝገብ ቅድስት የተባለች 17ኛ ተከሳሽ ግን እራሳቸውን ለመንከባከብ አቅም የሌላቸው የአራት ልጆች እናት መሆኗን ተከትሎ የህጻናቶች የቤተሰብን እንክብካቤ የማግኘት ህገመንግስታዊ የመብት ድንጋጌዎችን ታሳቢ በማድረግ እና ተከሳሿ የዋስትና ግዴታዋን አክብራ ልትቀርብ ትችላለች የሚል ግምት በፍርድ ቤቱ ተይዞ በ50 ሺህ ብር ዋስትና በማስያዝ ከስር እንድትፈታ በሙሉ ድምፅ ብይን ሰጥቷል።
የዋስትና ጥያቄያቸው ውድቅ የተደረገባቸው 19 ኙ ተከሰሶች ወደ አዲስ አበባ ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ ታዝዟል።
በዐቃቤ ሕግ የሚቀርቡ የምስክሮችን ዝርዝር ከምስክር ጥበቃ አዋጅ አንጻር መታየት አለበት ወይስ የለበትም የሚለውን ነጥብ በሚመለከት ክርክር ለማከናወን ለሃምሌ 20 ቀን 2015 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል።
በሌላ በኩል ተከሳሾቹ የታገደባቸው የባንክ ሒሳብ ለቤተሰብ ቀለብና የልጆች ትምህርት ቤት ክፍያ ለማከናወን እንዲችሉ እግዱ እንዲነሳላቸው ባቀረቡት አቤቱታ ላይ በቀጣይ ቀጠሮ ብይን እንደሚሰጥ በችሎቱ ተገልጿል።
በታሪክ አዱኛ