አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል 7 ሚሊየን 257 ሺህ ብር ግምት ያለው ሀብት እንዲሁም 56 ሺህ 900 ካሬ ሜትር የከተማና የገጠር መሬት ከምዝበራ ማዳን መቻሉን የክልሉ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
ያለአግባብ ሊመዘበር የነበረ 7 ሚሊየን 257 ሺህ 269 ብር ከ08 ሳንቲም ግምት ያለው ሀብት ማትረፍ እንደቻለ ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡
56 ሺህ 900 ካሬ ሜትር መሬትም ከምዝበራ ማዳን እንደተቻለ የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ይበልጣል ታደሰ ተናግረዋል፡፡
በክልሉ ሕግና መመሪያን ያልተከተሉ ብልሹ አሰራሮች አሉ የሚሉ 573 ጥቆማዎች ከህብረተሰቡ እንደተሰጠ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልጸዋል፡፡
ከጥቆማዎች ውስጥ 58 ጥቆማዎች በኮሚሽኑ አስቸኳይ የሙስና መከላከል ስራ የተፈቱ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
ኮሚሽኑ በተለይ በሂደት ላይ ያሉ ችግሮች ላይ መስራትና ማስቆም እንደሚችል ጠቅሰው፥ ሂደቱ ያለቀ ጉዳይ ደግሞ ወደ ፖሊስ ኮሚሽን እንደሚላክ አስረድተዋል፡፡
በቀጣይም ኮሚሽኑ በክልሉ ውስጥ ከሕግና መመሪያ ውጭ ያሉ የማጭበርበር ድርጊቶች ላይ በሁሉም ቦታ ገብቶ እንደሚሰራ አመላክተዋል፡፡
በተቋማት ውስጥ ከሕግ ውጭ እየተሰሩ ያሉ አሰራሮችን ለማስቆም ህብረተሰቡ በማስረጃ ላይ የተደገፈ ጥቆማ በመስጠት የሀገርንና የህዝብን ሀብት ለማዳን ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በየሻምበል ምህረት