አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ጣሊያን ከኢትዮጵያ ጋር የኢኮኖሚ ትብብሯን ይበልጥ የማጠናከር ፍላጎት እንዳላት የጣሊያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ኤድሞንዶ ቺሬሊ ገለፁ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ከጣሊያን አቻቸው ኤድሞንዶ ቺሬሊ ጋር ተወያይተዋል።
ውይይታቸው በዋናነት የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በሚጠናከርበት ጉዳይ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው ተብሏል።
በዚህም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ረጅም ዘመናት ያስቆጠረ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ሀገራቱ ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከጣሊያን ጋር ያላትን ሁለንተናዊ የትብብር ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እንደምትሻ አምባሳደር ብርቱካን ተናግረዋል።
ጣሊያን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር ለማጠናከር እያከናወነች ያለውን ስራም አድንቀዋል።
የጣሊያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ኤድሞንዶ ቺሬሊ በበኩላቸው÷ ጣሊያን ከኢትዮጵያ ጋር የኢኮኖሚ ትብብሯን ይበልጥ የማጠናከር ፍላጎት አላት ብለዋል።
የሽብርተኝነት እንቅስቃሴን በመታገልና ህገ ወጥ ስደትን በመከላከል ረገድ በጋራ ለመስራት ቁርጠኛ እንደሆኑ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡