የሀገር ውስጥ ዜና

በኢትዮጵያ የንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፉን ለማቀላጠፍ የግሉ ዘርፍ የነቃ ተሳትፎ ወሳኝ ነው ተባለ

By Alemayehu Geremew

July 25, 2023

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፉን ለማቀላጠፍ የግሉ ዘርፍ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚገባው የንግድና ቀጣናዊ ትሥሥር ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከንግድና ቀጣናዊ ትሥሥር ሚኒስቴርና ከፓን አፍሪካ ንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ጋር በመሆን የምክክር መድረክ አዘጋጅቷል።

ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ቀናት የሚካሄደው መድረክ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ፣ ቱሪዝም እና ዲጂታል ግብይት ላይ ትኩረት ያደርጋል ተብሏል፡፡

በመድረኩ የግልና የመንግስት ተቋማት እንዲሁም ተወካዮች እየተሳተፉ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

መድረኩ የግሉ ዘርፍ የሚያጋጥሙት መሰረታዊ ችግሮች ላይ መክሮ መፍትሄዎች ያመላክታልም ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በልሁ÷ ከግሉ ዘርፍ በንግድ ሥራ ላይ የሚሳተፈው ማኅበረሰብ ፈጣንና ምቹ አገልግሎት እንዲያገኝ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ኢንጂነር መላኩ እዘዘውም÷ የግብርና ምርቶችን በማቀነባበር ላይ የተሰማሩ የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ እንዲሁም የሀገር ውስጥ ምርት እንዲያድግ ወሳኝ ቢሆንም የሚፈለገው ደረጃ ላይ አልደረሰም ብለዋል።

የጥሬ ዕቃ በሚፈለገው መጠን አለመገኘቱ፣ ማቀነባበር እና ምርት አስተሻሸግ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች፣ የገበያ አማራጮች አለመስፋት፣ የመሰረተ ልማት አለመሟላትና የፋይናንስ እጥረቶች የዘርፉ ማነቆዎች መሆናቸውንም አመከላክተዋል፡፡

የግብርና ሚኒስትር ደኤታ ዶክተር ሶፊያ ካሳ በበኩላቸው÷ የግብርና ግብዓቶች ላይ ድጎማ ማድረግ፣ አርሶ አደሮች በኩታ ገጠም እንዲያርሱ ማድረግና ዘመናዊ የግብርና መሳሪያዎችን በማቅረብ በኩል ሁሉን አቀፍ ጥረቶች በመደረግ ላይ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ደኤታ ታረቀኝ ቡሉሉታ÷ የግል ባለሐብቱን የሚያሳትፉ 17 የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሰራ እንደሆነ ጠቅሰው፤ የቡሬ፣ ቡልቡላ እና ይርጋለም የግብርና ማቀነባበሪያ ፓርኮችም ወደ ሥራ መግባታቸውን ገልጸዋል።

ከምርት አስተሻሸግ፣ ከወጪና ገቢ ንግድና የጥሬ እቃ አቅርቦት ጋር የሚስተዋሉ ችግሮችንም ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።