የሀገር ውስጥ ዜና

ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር) ከፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ መከሩ

By ዮሐንስ ደርበው

July 26, 2023

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በሀገራዊ ሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡

በውይይታቸውም÷ ሁለቱ መሪዎች በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የቆየ እና ታሪካዊ ግንኙነት በማጠናከር የንግድ ግንኙነታቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በሚያስችላቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡

በተጨማሪም በግብርና እና በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ዙሪያ በትብብር ለመሥራት ያላቸውን ቁርጠኝነት መግለጻቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ዛሬ ረፋድ ላይ በኮንስታንቲኖቭስኪ ቤተ መንግሥት በፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

ፕሬዚዳንት ፑቲን ላደረጉልን አቀባበል እና ላካሄድነው ግልጽ ውይይት አመሰግናለሁ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልጸዋል፡፡

ታሪካዊ ትሥሥራችንን መሠረት አድርገን ኢትዮጵያ እና ሩሲያ የሁለትዮሽ ግንኙነታችንን እና ኢኮኖሚያዊ ትብብራችንን ማሳደግ እንቀጥላለን ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከ2ኛው የሩሲያ-አፍሪካ የመሪዎች ጉባዔ ቀድመው ለሥራ ጉብኝት መግባታቸው ይታወሳል።