የሀገር ውስጥ ዜና

በአማራ ክልል 4 ሺህ 648 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ በሕገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወር ተያዘ

By Melaku Gedif

July 27, 2023

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ከ4 ሺህ 648 ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ በሕገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወር መያዙን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ አጀበ ስንሻው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷በአማራ ክልል የተፈጠረው የአፈር ማዳበሪያ እጥረት አርሶ አደሮችን ለአላስፈላጊ ወጪ ዳርጓል።

በክልሉ የቀረበው የአፈር ማዳበሪያ ከአርሶ አደሩ ፍላጎት ጋር አለመጣጣሙ ለተፈጠረው ችግር ቀዳሚ መንስኤ መሆኑን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ሕገ ወጦች የተፈጠረውን የአፈር ማዳበሪያ እጥረት እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ችግሩን ይበልጥ አወሳስበውታል ነው ያሉት።

የሕገ ወጦችን ድርጊት ለመቆጣጠርም በክልሉ በየደረጃው በሚገኙ መዋቅሮች ግብረ ሃይል ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

በዚህም ከ4 ሺህ 648 ኩንታል በላይ ሕገ ወጥ የአፈር ማዳበሪያ መያዙን ጠቁመው÷ በድርጊቱ የተሳተፉ በርካታ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አንስተዋል።

ከተጠርጣሪዎች መካከል ፍርድ ቤት ቀርበው ውሳኔ የተላለፈባቸው እና ምርመራ እየተጣራባቸው የሚገኙ እንዳሉ አስረድተዋል።

በሕገ ወጥ የአፈር ማዳበሪያ ዝውውሩ የቀበሌ አመራሮች፣ ባለሙያዎች፣ ነጋዴዎች እና ሌሎች አካላት መሳተፋቸውን አረጋግጠዋል።

ሕብረተሰቡ መሰል ሕገ ወጥ የአፈር ማዳበሪያ ዝውውርን ሲመለከት ለሚመለከታቸው የጸጥታ አካላት እንዲጠቁም ጥሪ ቀርቧል፡፡

በአማራ ክልል እስካሁን 3 ነጥብ 8 ሚለየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለእርሶ አደሩ መሠራጨቱን አቶ አጀበ ተናግረዋል።

በመላኩ ገድፍ