የሀገር ውስጥ ዜና

የሩሲያ የግብርና ግብዓት አምራቾች በአፍሪካ ምርታማነትን ለማሳደግ ድጋፍ እንደሚያደረጉ ገለጹ

By Mikias Ayele

July 27, 2023

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሩሲያ የግብርና ግብዓት አምራቾች የአፍሪካ ሀገራት የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ እያደረጉት ያለውን ጥረት ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆናቸውን ገለጹ።

በሁለተኛው የሩሲያ- አፍሪካ የምጣኔ ሃብት እና ሰብዓዊ ጉዳዮች ጉባኤ ላይ “የሩሲያ አፍሪካ ትብብር ለግብርና ምርታማነት” በሚል መሪ ሃሳብ የጎንዮሽ ምክክር መድረክ ተካሂዷል፡፡

በመድረኩ የአፍሪካ ሀገራት የግብርና ዘርፍ ተወካዮች፣ የሩሲያ የግብርና ባንክ ተወካዮች እና የአምራች ድርጅቶች ሃላፊዎች በአፍሪካ የሚታየውን የግብርና ግብዓት እጥረት መቅረፍ በሚቻልበት አግባብ ላይ መክረዋል።

የሩሲያ ግብርና ባንክ ተወካይ ኦሌግ ኦዜሮቭ÷ ሩሲያና አፍሪካ በግብርናው ዘርፍ መተባበር የሚችሉባቸው በርካታ መንገዶች እንዳሉ ጠቅሰው÷ ይህንን ጥረት ለማገዝ ባንኩ ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል።

የግብርና ግብዓት አምራቾች በበኩላቸው÷ለአፍሪካ የግብርና ስነ-ምህዳር ተስማሚ የሆኑ እና ረጅም የአገልግሎት ዘመን ያላቸውን ዘመናዊ መሳሪዎች እና የአፈር ማዳበሪያ በተመጣጣኝ ዋጋ እንደሚያቀርቡ  ገልፀዋል፡፡

በተጨማሪም የአርሶ አደሮችን ክህሎት ማሳደግ የሚያስችሉ ፕሮጀክቶችን እንደሚተገብሩ አምራቾቹ ተናግረዋል።

 

በወንደሰን አረጋኸኝ