የሀገር ውስጥ ዜና

ዜጎች ራሳቸውን ለጉበት በሽታ አጋላጭ ከሆኑ መንስኤዎች ሊጠብቁ ይገባል – ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ

By Shambel Mihret

July 28, 2023

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ዜጎች ራሳቸውን ለጉበት በሽታ አጋላጭ ከሆኑ መንስኤዎች መጠበቅ እንዳለባቸው የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ ገለጹ።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ13ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ9ኛ ጊዜ “የጉበት ጤና ለጤናማ ሕይወት” በሚል መሪ ሀሳብ እየተከበረ ያለውን የጉበት በሽታ ቀንን አስመልክቶ ዶ/ር ደረጄ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

የጉበት በሽታ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲሁም በኢትዮጵያ ከፍተኛ የጤና መቃወስ ከሚያስከትሉ በሽታዎች ውስጥ አንዱ መሆኑን ዶ/ር ደረጄ ገልጸዋል።

የበሽታው መንስኤ ከሆኑት ውስጥም በሽታው ካለባቸው ሰው ጋር ልቅ የሆነ የግብረ ስጋ ግንኙነት መፈጸም እና አደንዛዥ እጽ መጠቀም ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።

አብዛኛው ማህበረሰብ የጉበት በሽታን አስቀድሞ ለመከላከል ወደ ሕክምና የመሄድ ልምድ እንዳላጎለበተ አመልክተው፤ ዜጎች ራሳቸውን ለጉበት በሽታ አጋላጭ ከሆኑ መንስኤዎች ሊጠብቁ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ሚኒስቴሩ የጉበት በሽታ ስርጭትን ለመከላከል ለማህበረሰቡ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ እያከናወነ ቢሆንም አሁንም ሰፊ ስራ ማከናወን እንደሚገባ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በተጨማሪም ታማሚዎች ተገቢውን የሕክምና አገልግሎት በጤና ተቋማት እንዲያገኙ እና አስፈላጊውን መድኃኒት ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።