አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ለሁለት ቀናት የሚካሄደው የዓለም አቀፍ የጭነት አስተላላፊዎች ማኅበራት ፌዴሬሸን /ፊያታ/ ጉባዔ ዛሬ በአዲስ አበባ ተጀምሯል፡፡
በመድረኩ የተገኙት የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) ÷የዓለም አቀፍ የጭነት ጉባዔው በአዲስ አበባ መካሄዱ ኢትዮጵያ በዘርፉ ጥሩ እመርታ ለማሳየቷ አመላካች ነው ብለዋል ፡፡
ጉባዔው በኢትዮጵያ ሲካሄድ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑንም ሚኒስትሩ ገልፀዋል፡፡
የጭነት ማስተላለፉ ለሀገር ኢኮኖሚ ግብዓትና ሸቀጦችን ወደ ገበያ ለማቅረብም ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለውም አስረድተዋል፡፡
ውይይቱ በጭነት ምልልሱ የሚታዩ ችግሮች በመለየት የመፍትሔ አቅጣጫ ለማመላከት ያለመ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
ዓለም አቀፍ የጭነት አስተላላፊዎች ማኅበራት ፌዴሬሽን 100ኛ ዓመት በዓልን በፈረንጆቹ 2026 በኢትዮጵያ እንዲያዘጋጅ ጥያቄ መቅረቡንም ጠቁመዋል።
የፌዴሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር ጄነራል ስቴፈን ግራበር (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ በሎጂስቲክስ ዘርፍ ባለፉት ዓመታት ጠንካራ የሚባሉ ሥራዎችን መሥራቷን ገልፀዋል።
በኢትዮጵያ የሎጂስቲክስ ዘርፉ ይበልጥ እንዲጠናከር የበኩላቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ጉባኤው ኢትዮጵያ በአካባቢው ሀገራት በአየር ጭነት ትራንስፖርት ያላትን ስትራቴጂካዊ ሚና ለማስገንዘብ መልካም ዕድል እንደሚፈጥርም ተገልጿል፡፡