የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ አጋርነት የጋራ ተጠቀሚነትን በሚያጎለብት መልኩ ተጠናክሮ ይቀጥላል- አቶ ደመቀ መኮንን

By Shambel Mihret

July 31, 2023

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ ግንኙነት የሀገራቱን ሕዝቦች ተጠቃሚነት በሚያጎለብት መልኩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለፁ።

አራተኛው የኢትዮ-ደቡብ አፍሪካ የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብሰባ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በመድረኩ አቶ ደመቀ መኮንን፣ የደቡብ አፍሪካ የዓለም አቀፍ ግንኙነቶችና ትብብር ሚኒስትር ናሌዲ ፓንዶር (ዶ/)ር እንዲሁም የሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ተሳትፈዋል።

በስብሰባው የሁለቱ ሀገራት በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በሳይንስ፣ በኢኖቬሽን፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በባህልና በሌሎች መስኮች የተፈራረሟቸውን የሁለትዮሽ ሥምምነቶች የአፈጻጸም ደረጃ ተገምግሟል።

አቶ ደመቀ መኮንን በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ትብብር ማጎልበት በሚቻልበት ጉዳዮች ላይ ውይይት ተደርጓል ብለዋል።

እስካሁን ያለው የትብብር ሥምምነቶች አፈፃፀም አጥጋቢ መሆኑን ገልጸው በቀጣይም ይህንን አጋርነት ይበልጥ ለማጠናከር ተቀራርቦ ለመሥራት ሥምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል።

ከዚህ አኳያ የተካሄደው የሁለቱ ሀገራት የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብሰባ ስኬታማ ነበር ነው ያሉት።

የደቡብ አፍሪካ የዓለም አቀፍ ግንኙነቶችና ትብብር ሚኒስትር ናሌዲ ፓንዶር (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ሁለቱ ሀገራት በተለያዩ የትብብር መስኮች ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸው ጠቁመዋል።

ይህንንም አጋርነት በቀጣይ ይበልጥ አጠናክሮ ለመቀጠል የጋራ መግባባት ላይ መደረሱን ነው የገለጹት።

ጎን ለጎንም ተለዋዋጭ በሆነው ዓለም ተወዳዳሪ ሆኖ ለመውጣት የባለ ብዙ ወገን ተቋማት ላይ አፍሪካ ድምጽ እንዲኖራት በጋራ መሥራት ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።