የሀገር ውስጥ ዜና

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት አጃይ ባንጋ ጋር ተወያዩ

By Melaku Gedif

July 31, 2023

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት አጃይ ባንጋን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) እና ልዑካቸው ባደረጉት የሁለትዮሽ ውይይት በአጠቃላይ የኢትዮጵያን ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ ላይ ገለጻ አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)÷”የዓለም ባንክ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን የትብብር አድማስ በማስፋት ለኢኮኖሚ እድገታችን በኮንሴሽናል ፋይናንስ፣ በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን በኩል ጠንካራ የኢንቨስትመንት ፋይናንስ አቅርቦት እንዲኖር አስተዋጽኦ ይኖረዋል” ብለዋል፡፡

በተጨማሪም የዓለም ባንክ ትብብር የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳዎችን በመደገፍ ዘላቂነት ያለው  አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አንስተዋል፡፡

አጃይ ባንጋ በበኩላቸው÷በሀገር ውስጥ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዙ ፈተናዎች ቢያጋጥሙም ኢትዮጵያ ለቁልፍ የልማት ግቦች የሰጠችውን ትኩረት አድንቀዋል፡፡

የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት አጃይ ባንጋ÷ለሁለት ቀናት ጉብኝት ዛሬ ከሰዓት አዲስ አበባ መግባታቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡