አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ለሽብር ተግባር 50 የእጅ ቦምቦች እና 58 የቦምብ ፊውዞችን በመያዝ ሲንቀሳቀሱ ተይዘዋል የተባሉ ግለሰቦች ላይ የ14 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተፈቀደ።
የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን መርማሪ ከዚህ በፊት በተሰጠው የ14 ቀን ጊዜ ቀጠሮ የሰራውን የምርመራ ውጤትና የተጠርጣሪዎችን የመከራከሪያ ነጥብን ተመልክቶ ነው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ የፈቀደው።
ዛሬ ለሁለተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት የቀረቡት ተጠርጣሪዎች አብዱ መላኩ ቡሾ፣አማኑኤል ግርማ ተሲሳ እና ደጋጋ ፈቀደ ወለጋ ናቸው።
መርማሪ ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት በአሸባሪነት የተፈረጀውን የሸኔ የሽብር ቡድን የአባልነት መታወቂያ በመያዝ ፣የሽብር ቡድኑ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ በመገናኘት፣ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን እና አልባሳትን በማቀበል የሽብር ቡድኑን አላማ ለማስፈጸም ሲንቀሳቀሱ እንደነበር አመላክቷል፡፡
ተጠርጣረዎቹ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ ወረዳ 14 ተከራይተው በሚኖሩበት መኖሪያ ቤት ውስጥ ለሽብር ተግባር የሚውል 50 (ኤፍ ዋን) የእጅ ቦምብና 58 የቦንብ ፊውዞችን ገዝተው ሲንቀሳቀሱ በተደረገ ክትትል ሐምሌ 7 ቀን 2015 ዓ.ም እጅ ከፍንጅ ተይዘው ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ቀርበው የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ መሰጠቱ ይታወሳል።
ፍርድ ቤቱም በዚህ መልኩ ለመርማሪ ፖሊስ ከዚህ በፊት በሰጠው የምርመራ ጊዜ ውስጥ የተሰሩ የምርመራ ውጤቶችን ዛሬ ከሰዓት በኃላ ተመልክቷል።
መርማሪ ፖሊስ በተሰጠው የ14 ቀን ጊዜ ውስጥ የተጠርጣሪዎችን የተከሳሽነት ቃልና የ4 ምስክሮችን የምስክርነት ቃል መቀበሉን፣ ከተወሰኑ ባንኮች በተጠርጣሪዎቹ ሒሳብ ከፍተኛ የገንዘብ ዝውውር መኖሩን የሚያመላክቱ የማረጋገጫ ማስረጃዎችን በማምጣት ከምርመራ መዝገቡ ጋር ማያያዙን፣ ኢትዮ ቴሌኮምን ማስረጃ መጠየቁንና የፎረንሲክ ማስረጃዎችን ማስመጣቱን ገልጿል።
የቴክኒክ ማስረጃ ከሚመለከተው አካል የማስመጣት ፣የተጨማሪ ምስክሮችን ቃል መቀበል፣ ግብረ አበር ተከታትሎ የመያዝ ስራና ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያላቸውን የተለያዩ ማስረጃዎች የማስመጣት ስራዎች እንደሚቀረው ገልጾ÷ ተጨማሪ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።
ተጠርጣሪዎቹ ከወንጀሉ ጋር ግንኙነት እንደሌላቸው ገልጸው በመከራከር፤ የዋስትና መብታቸው እንዲከበር ጠይቀዋል።
መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ÷ የተጠረጠሩበት የሽብር ወንጀል ውስብስብ እንዲሁም ህዝብና መንግስትን አደጋ ላይ የሚጥል ተግባር በመሆኑ የዋስትና ጥያቄያቸውን በመቃወም ተከራክሯል።
የግራ ቀኙን ክርክር የተመለከተው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ተጠርጣሪዎች ከተጠረጠሩበት ወንጀል ውስብስብነት አንጻር ተጨማሪ ምርመራ መከናወን እንዳለበት በማመን የተጠርጣሪዎችን የዋስትና ጥያቄ ለጊዜው ውድቅ አድርጓታል።
ለተጨማሪ የማጣሪያ ምርመራም ለፖሊስ የ14 ቀን ጊዜ ፈቅዷል።
ታሪክ አዱኛ