አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያና የአፍሪካ ልማት ፈንድ ለስንዴ ምርትና ምርታማነት ማሻሻያ የሚውል የ84 ነጥብ 3 ሚሊየን ዶላር ወይም የ4 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር የልማት ድጋፍ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡
ስምምነቱን በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የገንዘብ ሚነስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ እንዲሁም የአፍሪካ ልማት ፈንድን በመወከል በምስራቅ አፍሪካ የአፍሪካ ልማት ባንክ ምክትል ዳይሬክተር አብዱል ካማራ (ዶ/ር) ፈርመውታል፡፡
ከልማት ደጋፉ ውስጥ 54 ሚሊየን ዶላር ከአፍሪካ ልማት ፈንድ፣ 20 ሚሊየን ዶላር ከኔዘርላንድስ መንግስት፣ 10 ሚሊየን ዶላር ኦ ሲ ፒ አፍሪካ ከተባለ ድርጅት እንዲሁም ቀሪውን 300 ሺህ ዶላር ግሎባል ሴንተር ፎር አዳብቴሽን ከተባለ ተቋም የተገኘ መሆኑ ታውቋል፡፡
የልማት ድጋፉ በአነስተኛ እርሻ የስንዴ አምራች አርሶ አደሮችን ምርትና ምርታማነት ለማሻሻል የሚውል እንደሆነም ተገልጿል፡፡
ድጋፉ ይህንን ዕውን ለማድረግ ከአካባቢ ጋር ተስማሚ የስንዴ ምርት ለማምረት፣ የገበያ መሰረተ ልማቶችንና ትስስርን ለማሳደግ እንዲሁም በዘርፉ ያሉ ፕሮጀክቶችን ለማስተዳደር የሚውል ነው ተብሏል፡፡
ይህ ድጋፍ በተለይ የሀገር ውስጥ የስንዴ ፍላጎትን በሀገር ውስጥ ምርት ለማሟላት የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ሲሆን÷ በቀጣይ አምስት ዓመታት ውስጥ የሚተገበር እንደሚሆን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!