የሀገር ውስጥ ዜና

የመንግስትን ተሽከርካሪ በመጠቀም ከባድ የጦር መሳሪያዎችን በመጫን ለሽብር ቡድን ሊያስረክቡ ነበር የተባሉ ተጠርጣሪዎች ፍርድ ቤት ቀረቡ

By Feven Bishaw

August 04, 2023

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 28 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የመንግስትን ተሽከርካሪ በመጠቀም ከባድ የጦር መሳሪያዎችን በመጫን ለሽብር ቡድን ሊያስረክቡ ነበር የተባሉ ተጠርጣሪዎች ፍርድ ቤት ቀረቡ።

ተጠርጣሪዎቹ አህመድ እንድሪስ፣ አስራት ዲባባ፣ ሶሪ ተካልኝ፣ ጎንፋ ሶር ፣ አቡበከር ፈንታሁን ፣ መሐመድ እንድሪስ እና ወይዘሮ ፈይዟ እንድሪስ የተባሉ ናቸው።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት በሁለት መዝገብ በትናንትናው ዕለት በነበረ ጊዜ ቀጠሮ እና በዛሬው ዕለት በነበረ ጊዜ ቀጠሮ በሁለት መዝገብ የተጠርጣሪዎችን ጉዳይ ተመልክቷል።

ተጠርጣሪዎቹ የጦር መሳሪያ በመደበቅ፣ በተሽከርካሪ በመጫን እና ለሌላ የሽብር ቡድን አካል ለማቀበል በሚደረግ እንቅስቃሴዎች ያላቸው ሚና ተጠቅሶ በጊዜ ቀጠሮ መዝገብ ቀርቧል።

በዚህ መሰረት ተጠርጣሪዎቹ የሸኔ የሽብር ቡድን ተልዕኮ ለማስፈጸም ተልዕኮ ተቀብለው ለሽብር ቡድኑ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን ማለትም፥ 2 ስናይፐር ፣ 1 አር ቢ ጅ፣ 5 የአር ቢ ጅ ጥይቶች (ቅንቡላ) ፣ 28 የእስናይፐር ካርታ፣ 8 የተለያዩ ጥይቶች፣ 5 ወታደራዊ አልባሳት ለማቀበል የአዋሽ ፈንታሌ የፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ ተሽከርካሪ ላይ በመደበቅ ኦሮሚያ ክልል ለሚገኘው ለሽብር ቡድኑ ለማድረስ ከአዋሽ ተነስተው በአዲስ አበባ በኩል ሲንቀሳቀሱ ሰበታ ላይ በፀጥታ ኃይሎች ሐምሌ 24 ቀን 2015 ዓ.ም መያዛቸውን መርማሪ ፖሊስ ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ አስረድቷል።

መርማሪ ፖሊስ የጀመረውን የምርመራ ስራ በሰውና በሰነድ ማስረጃ አጠናቆ ለማቅረብ የ14 ቀን የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቋል።

ከተጠርጣሪዎቹ መካከል አህመድ እንድሪስ የተባለው ግለሰብ ከአዋሽ ወደ አዲስ አበባ ወንድሙን ለመጠየቅ እንዲያመጣው ጠይቆ አቡበከር ፈንታሁን የሚባለው ተጠርጣሪ በሚያሽከረክረው መኪና መምጣቱን ጠቅሶ ስለወንጀሉ የሚያውቀው ነገር እንደሌለ ገልጿል።

በዚህ ጊዜ ጊዜ ቀጠሮ መዝገቡን የተመለከቱት የችሎቱ ዳኛ ግለሰቡ በተጫነበት ተሽከርካሪ ውስጥ የጦር መሳሪያ መኖሩን እንደሚያውቅ እና እንደማያውቅ የማረጋገጫ ጥያቄ አቅርበዋል።

በዚህ ጥያቄ መነሻ ተጠርጣሪው በመኪናው ውስጥ በመጀመሪያ ጦር መሳሪያ መኖሩን አለማወቁን ጠቅሶ በኋላ ላይ ግን በቁጥጥር ስር ሲውሉ መኪናው በፀጥታ ኃይል ሲፈተሽ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች ከመኪናው ውስጥ ሲወጣ መመልከቱን ገልጿል።

አስራት ዲባባ እና ሶሪ ተካልኝ የተባሉ ተጠርጣሪዎች በበኩላቸው የኤፍ ኤስ አር አሽከርካሪና ረዳት በመሆን ውሃ በማከፋፈል ሽያጭ ስራ እንደሚሰሩ ገልጸው ከወንጀሉ ጋር ግንኙነት የለንም በማለት ተከራክረዋል።

ሌላኛው ጎንፋ ሶር የተባለው ተጠርጣሪ ደግሞ ከአየር ጤና ወደ አውቶቡስ ተራ ሰው ለመቀበል ሄዶ ለጥያቄ ትፈለጋለህ ተብሎ በቁጥጥር ስር መዋሉን በመግለጽ ከወንጀሉ ጋር ግንኙነት እንደሌለው በመጥቀስ የአራት ልጆች አባት መሆኑንም አስረድቷል።

በሌላ መዝገብ ከቀረቡት ተጠርጣሪዎች መካከል አቡበከር ፈንታሁን የተባለው ግለሰብ የአዋሽ ፈንታሌ ፀጥታ ዘርፍ የመንግስት ተሽከርካሪ ሾፌር መሆኑን በመጥቀስ ገንዘብ ይከፈልሃል ተብሎ የጦር መሳሪያዎቹን እንዲያደርስ በግለሰብ ታዞ መሳሪያዎቹን በመደበቅ ጭኖ መምጣቱን እና በቁጥጥር ስር መዋሉን አምኖ ለችሎቱ አስረድቷል።

መሐመድ እንድሪስ እና ወይዘሮ ፈይዟ እንድሪስ የተባሉ ተጠርጣሪዎች ደግሞ እንደሚተዋወቁና የጋብቻ ዝምድና እንዳላቸው ጠቅሰው ከወንጀሉ ጋር ግንኙነት እንደሌላቸው በመግለጽ አብራርተዋል።

ሁሉም ተጠርጣሪዎች የዋስትና መብት ጥያቄ አቅርበዋል።

በዚህ ጊዜ የተጠርጣሪዎቹ ሚናን በሚመለከት መርማሪ ፖሊስ በዝርዝር አቅርቧል።

በዚህም ፖሊስ የጦር መሳሪያ በማምጣትና በመደበቅ መሐመድ እንድሪስ እና ወይዘሮ ፈይዟ እንድሪስ የተባሉ ተጠርጣሪዎች ዋና ተዋናይ መሆናቸውን በመግለጽ እነዚህ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ በተደረገ ፍተሻ ሌላ 750 ጥይቶች እንደተገኙባቸው የተሳትፎ ደረጃቸውን ጠቅሶ አብራርቷል።

ሌሎቹ ማለትም አቡበከር ፈንታሁን የተባለው ግለሰብ የአዋሽ ፈንታሌ ፀጥታ ዘርፍ የኮብራ መኪና ሾፌር ሆኖ እንደሚሰራና የጦር መሳሪያ ጭኖ አህመድ እንድሪስ ከተባለ ተጠርጣሪ ጋር በመሆን ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ለአስራት ዲባባ እና ሶሪ ተካልኝ ለማቀበል ሲሉ መያዛቸውን ጠቅሶ በዝርዝር አብራርቷል።

አስራት ዲባባ እና ሶሪ ተካልኝ የተባሉት ተጠርጣሪዎች ደግሞ የጦር መሳሪያዎቹን ከእነ አቡበከር ለመረከብና በኤፍ ኤስ አር ተሽከርካሪ በመጫን ለሽብር ቡድኑ የማቀበል ሚና እንዳላቸው መርማሪው ጠቅሷል።

አየርጤና ወደ አውቶቡስ ተራ በመሄድ ሰው ልቀበል በመጠባበቅ ላይ እንደነበርኩ ለጥያቄ ትፈለጋለህ ተብዬ ነው የተያዝኩት እንጂ የማውቀው ነገር የለም በማለት የተከሪከረው ጎንፋ ሶር የተባለው ተጠርጣሪን በሚመለከት ደግሞ መርማሪ ፖሊስ ግለሰቡ በስልክ የጦር መሳሪያው የት ቦታ ፣ መቼ ማምጣት እንዳለባቸው፣ ለማንስ ማስረከብ እንዳለባቸው በስልክ አቅጣጫ የሚመራና መረጃ የሚሰጣቸው ተጠርጣሪ መሆኑን ጠቅሶ ፖሊስ የግለሰቡን የተሳትፎ ሚናን በሚመለከት ማብራሪያ ሰጥቷል።

እንደ አጠቃላይ የጠየቁት የዋስትና ጥያቄን በመቃወም ቢወጡ ማስረጃ ሊያጠፉ እንደሚችሉ ስጋቱን ገልጾ ተከራክሯል።

በሁለት መዝገብ የግራ ቀኙን ክርክር የተከታተለው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ተጠርጣሪዎች ከተጠረጠሩበት የሽብር ወንጀል ውስብስብነት አንጻር የዋስትና ጥያቄያቸውን ውድቅ በማድረግ ለመርማሪ ፖሊስ የ14 ቀን ማጣሪያ ጊዜ ፈቅዷል።

በታሪክ አዱኛ